በመቀለ መጠጥ ቤት ውስጥ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ

ፍንዳታው የተከሰተበት መጠጥ ቤት
የምስሉ መግለጫ, ፍንዳታው የተከሰተበት መጠጥ ቤት
ታትሟል

ለአሸንዳ በዓል በርካታ እንግዶችን እያስተናገደች ባለችው የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት አራት ሰዎች ሲሞቱ 20 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደረሰባቸው።

ይህ ለሰዎች ሞት እና መጎዳት ምክንያት የሆነው የቦምብ ፍንዳታ የደረሰው በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ነው ተብሏል።

ትናንት ሐሙስ ሌሊቱ 8 ሰዓት ከ45 ላይ የደረሰው የቦምብ አደጋ በከተማዋ ውስጥ ባለው በቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15 በሚገኝ ዳእሮ በሚባል መጠጥ ቤት ውስጥ እንደሆነ ከፍንዳታው የተረፉ ሰዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ይህ አደጋ የደረሰው አንድ ግለሰብ ከመጠጥ ቤቱ ውስጥ ከምትሠራ አስተናጋጅ ጋር የተፈጠረ አለመግባባትን ተከትሎ እንደሆነ የመቀለ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር ወልዳይ መውጫ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአይደር ሆስፒታል በበኩሉ ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ 20 የቆሰሉ ነዋሪዎችን እንደተቀበለ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከልም አምስቱ በጽነ መቁሰላቸውን እና ሌሎቹ ግን ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው የሆስፒታሉ የድንገተኛ ሕክምና አስተባባሪ አበበ ሃብቱ ለቢቢሲ አስረድቷል።

በቦምብ ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ከሠራዊት የተቀነሰ ታጋይ እንደሆነ እና ድርጊቱንም ኤፍ ዋን በተባለው የእጅ ቦምብ በመጠጥ ቤቱ ውስጥ በማፈንዳት መፈጸሙ ተገልጿል።

ነገር ግን ይህንን አደጋ ያደረሰው ግለሰብ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር አለመዋሉን የመቀለ ፖሊስ ገልጾ፣ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል።

በፍንዳታው ወጣት እግሩ እና እጁ ላይ መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት አብረሃም ተገኝ የተባለው ወጣት፣ ጥቃቱ ሲፈጸም በዓሉን በማስመልከት ከጓደኞቹ ጋር እየተዝናና እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በፍንዳታው ምክንያት ከፍተኛ ድምጽ ከመስማት ውጪ፣ ከዚያ በኋላ በመዝናኛ ስፍራው ምን እንደተከሰተ አላወቅኩም” ብሏል።

በዚህ አደጋ አንገቷን እና ደረቷ አካባቢ ጉዳት የደረሰባት ሜሮን ሙሴ ደግሞ “አሸንዳን ምክንያት በማድረግ ለመዝናናት ነበር የወጣነው። ድንገት ከባድ የፍንዳታ ድምጽ ሰማን። ከዚያ በኋላ ራሴን ስለሳትኩ ምን እንደተፈጸመ ትዝ አይለኝም” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።