በጋርዲዮላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ኃያልነት የተሸጋገረው ሻምፒዮኑ ማንቸስተር ሲቲ

የፎቶው ባለመብት, GETTY
ማንቸስተር ሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ እያሳየ ባለው የበላይነት ምክንያት በታሪካዊነት ለተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ያነሳው የሊጉ ዋንጫ ለብዙዎች ምንም የተለየ ነገር የለውም የሚያስብል ሆኗል።
ሲቲ ካለፉት ሰባት ዓመታት በስድስቱ የበላይ ሆኖ የሊጉ የፍጻሜ ቀን ጨዋታ ላይ ደርሷል። ዘንድሮ ደግሞ ዌስት ሃምን በማሸነፍ ዋንጫውን ወደተለመደው ቦታው ወስዶታል።
አይበገሬው የፔፕ ጋርዲዮላ ድል ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ አይነኬ መሆኑን በድጋሚ አሳይቷል።
ቡድኑ ለጫና የማይበገር ይመስላል። ድንጋጤ የሚፈጥረው ተልዕኳቸውን ሳያሳኩ ቢቀር ነበር።
ማንቸስተር ሲቲ ከስኬት ጋር የተቆራኘ ነው። በታህሳስ ወር በአስቶንቪላ ከተሸነፉ በኋላ 19ኙን አሸንፈው አራቱን አቻ ተለያይቷል። ይህ ሊያስገርም የሚችለው ጥቂቶችን ብቻ ነው።
በፋይናንስ አጠቃቀም ምክንያት በፕሪሚየር ሊጉ የቀረበበት 115 ክስ ከዚህ ድል እና ስኬት ጎን ለጎን ግን አንድ ነገር አብሮ ይነሳል። ሲቲ ግን ክሱን አጥብቆ አስተባብሏል።
ክሶቹ ከቀረቡበት 15 ወራት አልፈዋል። በዚህ ጉዳይ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ፍትህ ካልተሰጠ በቀር ቡድኑ ዋንጫ ባነሳ ቁጥር ጥርጣሬ እና ጫጫታ አብሮ ይነሳል።
መለኪያው እግር ኳስ ከሆነ ግን ምንም ክርክር የለውም።
የኮቪድ ወረርሽኝ ጥላውን ባጠላበት የ2019-20 የውድድር ዘመን ሊቨርፑል ዋንጫውን አሳክቷል።
የየርገን ክሎፑ ቡድን ከ30 ዓመታት በኋላ ዋንጫውን ወደ አንፊልድ የመለሰው በ18 ነጥብ ልዩነት ነበር ክብሩን የደፋው።
ከዚያ በኋላም ሊቨርፑል ጥረት አድርጓል። ይህንን ሁለት ዓመት ደግሞ አርሰናል መጣሁ መጣሁ ሲል ቢቆይም ከአስደናቂው ቡድን በላይ መሆን አልቻሉም።
በክሎፕ የሚመራው ሊቨርፑል ድንቅ የነበረ ቢሆንም በቂ ግን አልነበረም። ይህ የአሰልጣኙን ሚኬል አርቴታውን አርሰናልንም ይመለከታል።
ሲቲ በውድድር ዓመቱ መገባደጃ ላይ ማርሹን ይቀይራል። ባለቀ ሰዓት ጡንቻውን እያሳየ የሊቨርፑልን ልብ ደጋግሞ የሰበረበትን መንገድ ዘንድሮ ደግሞ አርሰናል ላይ ደግሞታል።
በውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ቀን ሊቨርፑልን ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ቀምተውታል።
በ2018-19 የውድድር ዓመት በብራይተን 4 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን በአንድ ነጥብ ልዩነት አንስተዋል። በ2021-22 ደግሞ 2 ለምንም በአስቶን ቪላ ሲመራ የነበረው ሲቲ ጨዋታው 14 ደቂቃ ሲቀረው አሸንፎ በድጋሚ ዋንጫውን ከክሎፕ እጅ ላይ ነጥቋል።
ይህ በ2011-12 እና 2013-14 በሮቤርቶ ማንቺኒ እና ማኑዌል ፔሌግሪኒ የተጀመሩ ልምዶች ናቸው ብንል እንኳን ጋርዲዮላ እና ተጫዋቾቹ የተለመደ እንዲመስል አድርገውታል።
ቡድኑ በየቦታው ጥራት ባላቸው ተጫዋቾች የተሞላ ነው። ኧርሊንግ ሃላንድ ከፊት፤ ኬቪን ደብሩይን ከመሐል ሆነው ቡድኑን ወደ ድል መርተውታል። ፊል ፎደን ደግሞ ከመሐል እየተነሳ ዘንድሮ 27 ኳሶችን ከመረብ በማገናኘት ታላላቆቹን ተጫዋቾች ተቀላቅሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሃላንድ በተለይም ደግሞ ደብሩይን በጉዳት ለረዥም ጊዜ ከሜዳ ርቀው ነበር። የሚተካቸው ግን አላጡም።
በ2022 የዓለም ዋንጫ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ጆስኮ ግቫርዲዮል ለወደፊቱ የመሐል ተከላካዩን ይመራል በሚል 77 ሚሊዮን ፓውንድ ተከፍሎበት የማንችስተር ስታዲየም ኢትሃድ ደረሰ።
ከመሐል ተከላካይነት ወደ ግራ ክንፍ ተከላካይነት ተዘዋውሮ ቢሰለፍም፤ መከላከል ብቻ ሳይሆን ፉልሃም እና ኖቲንግሃም ፎረስት ላይ ጎል ማስቆጠር እንደሚችልም አሳየ።
ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂው ኤደርሰን በጉዳት ከሜዳ ሲወጣ ተተክቶ የገባው ስቴፋን ኦርቴጋ ተተኪው መሆኑን ቶተንሃም ላይ ባስመዘገቡት ድል አስመስክሯል።
ሶን ሁንግ-ሚን አንድ ለአንድ ከበረኛው ጋር ሲገናኝ ለአርሰናል ደጋፊዎች ደስታ ልትሰጥ ከጫፍ የደረሰችውን እና ለፔፕ ጋርዲዮላ ደግሞ ባለማመን ሜዳ ላይ እንዲዘረር ያደረገችውን ዕድል ያመከነው ኦርቴጋ ነው።
አሰልጣኙ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ግብ ጠባቂውን የሳመበት መንገድ ምን ያህል እፎይታ የፈጠረች ኳስ እንዳደነ ያሳየ ነበር።
ቡድኑ ባለፈው ዓመት ያደረገው የተጫዋቾች ዝውውር ገና ፍሬ አልታየም። ቤልጂየማዊው ተጫዋች ጀረሚ ዶኩ ተሠርቶ ያላለቀ እንቁ ነው። ከዎልቭስ በ53 ሚሊዮን ፓውንድ ፈረመው ማቲያስ ኑኔዝ ተሳትፎው እምብዛም ነበር። ቡድኑ ተጋላጭ መሆኑን በውድድር ዓመቱ ያሳየባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ያም ተባለ ይህ ደጋፊዎቹ ደጋግመው እንደሚዘምሩት ግን ዋንጫውን ያነሳው ማን እንደሆነ መመልከት ብቻ በቂ ነው።
ከምንም በላይ የጋርዲዮላ ተጨዋቾች ተፎካካሪዎች ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና በመፍጠር፤ ዓይናቸውን ከዋንጫው ላይ ሳያነሱ ጫናዎችን መቋቋም የቻሉበት መንገድ ደጋግመው አሳይተዋል።
በ2018-19 የውድድር ዘመን ሲቲ 14 ተከታታይ ድሎች በማስመዘግብ ዋንጫውን ከሊቨርፑል ነጥቋል። የክሎፕ ቡድን በሻምፒዮኖቹ ብቻ ተሸንፎ 97 ነጥብ ማግኘቱ ዋንጫውን ለማንሳት በቂ አልነበረም። በ2021-22 የውድድር ዘመንም ተመሳሳይ ነበር።
ዘንድሮም አርሰናል በአስቶን ቪላ 2 ለምንም መሸነፉን ተከትሎ ሲቲ ውድድሩን በበላይን እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ይዞ ዘልቋል። ለዚህ የሲቲ ቡድን አንድ ዕድል ከሰጡ በብዙ እጥፍ አድርገው መውሰድን ይችሉበታል።
የጋርዲዮላ ቡድን ተሰጥኦ ባላቸው ተጫዋቾች ተሞልቷል። በውድድር ዘመኑ የሚገጥማቸውን ፍትጊያ ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ አዕምሮ ተጠቅመው በቀላሉ ወደ ፊት ይችላሉ።
እንደ አርሰናል እና ሊቨርፑል ላሉት ቡድኖች መጥፎው ዜና ሲቲ ለዋንጫ ያለው የማይጠገብ ፍላጎት በተከታታይ ስኬቶች አለመርካቱ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድን በዌምብሌይ ደግመው ካሸነፉ ለሦስተኛ ጊዜ የሊጉን እና የኤፍኤ ካፕን በጋራ ከፍ ማድረግ ይችላሉ።
ማንቸስተር ሲቲ ባለፈው ዓመት ያሳካውን የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍ ኤካፕ ዋንጫዎች በማንሳት የሦስትዮሽ ድሉን ዘንድሮ መድገም ባይችልም በእንግሊዝ ሊግ ኃያልነቱን ግን በድጋሚ አረጋግጧል።












