ኤንዞ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክብረ-ወሰን በሆነ ገንዘብ ቼልሲን ተቀላቀለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቼልሲ አርጀንቲናዊውን አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝ ክብረ-ወሰን በሆነ ገንዘብ ከቤነፊካ አዘዋወረ።
በአሜሪካዊው ባለሃብት የሚመራው ቼልሲ ለኤንዞ 107 ሚሊዮን ፓዎንድ በመክፈል፣ማንችስተር ሲቲ ጃክ ግሪሊሽን ለአስቶን ቪላ ያዘዋወረበትን ሪኮርድ ሰብሯል።
ቤነፊካ ኤንቮ ፈርናንዴዝን ከ7 ወራት በፊት ከአርጀንቲናው ክለብ ሪቨር ፕሌት በ10 ሚሊዮን ፓዎንድ ብቻ ነበር ያስፈረመው።
ቤነፊካ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ምርጥ ወጣቱ ተጫዋች የሚል ሽልማትን ያገኘውን አማካይ ተጫዋቹን ለቼልሲ መሸጡን አረጋግጧል።
ቼልሲ ለኤንዞ 107 ሚሊዮን ማውጣቱን ተከትሎ በጥር ወር የዝውውር መስኮት ለተጫዋቾች ዝውውር የከፈለውን ገንዘብ 288 ሚሊዮን አድርሶበታል።
ሰማያዊዎቹ ቼልሲዎች ከኤንዞ በተጨማሪ ለዩክሬናዊው የክንፍ ተጫዋች ሚካሄሎ ሞድሪች 90 ሚሊዮን ፓዎንድ የቀረበ ገንዘብ ከፍሏል።
ሰማያዊዎቹ ምንም እንኳ በጥር የዝውውር መስኮቱ ከፍተኛ ገንዘብ ለተጫዋች ግዢ ወጪ ያድርጉ እንጂ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከመሪው አርሰናል በ21 ነጥብ ርቀው 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የመጨረሻ ቀን ዝውውሮች
አርሰናል በዝውውር መስኮቱ ማብቂያ ዕለት ጣሊያናዊውን አማካይ ጆርጂኒዮን ከቼልሲ በ12 ሚሊዮን ፓዎንድ አስፈርሟል።መድፈኞቹን የብራይትን አማካዩን ካይሴዶ ለማስፈረም ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ በምትኩ ጣሊያናዊውን ወደ ኤሜሬትስ አስመጥተዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ የአማካዩን ክርስቲያን ኤሪክሰን ጉዳት ተከትሎ ኦስትሪያዊውን አማካይ ሳቢትዘር ከ ባየር ሙኒክ በውሰት አስፈርመዋል።
ሳውዝሃምፕተን ደግሞ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ገንዘብ ወጪ በማድረግ ጋናዊውን የክንፍ ተጫዋች ከፈረንሳዩ ክለብ አዘዋውረዋል።
ሳውዝሃምፕተን ለ20 ዓመቱ ወጣት ካማለዲን ሱሌይማን 22 ሚሊዮን ፓዎንድ ከፍለዋል።
ቶተነሃም ደግሞ ተከላከዩን ፔድሮ ፖሮ ከስፖርቲንግ ሊዝበን አዘዋውሯል።

የጥር ወር የክለቦች ከፍተኛ ወጪዎች
ቼልሲ በዚህ የውድድር መስኮት ከፍተኛውን ወጪ ያደረገ ክለብ ሆኗል።
የለንደኑ ክለብ ለአርጀንቲናዊው ኤንዞ ፈርናንዴዝ ለእንግሊዝ ሪኮርድ የሆነ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ከማዘዋወሩም በተጨማሪ ለዩክሬናዊው ሚካይሎ ሙድሪክ 89 ሚሊዮን ፓዎንድ ከፍለዋል።
የሊጉ መሪ አርሰናልም በዚህ በጥር ወር የዝውውር መስኮት ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ሰሜን ለንደን አስመጥቷል።
በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀን በ12 ሚሊዮን ፓዎንድ ጆርጂኒዮን ከቼልሲ ወስዷል። አርሰናል ለብራይተን አጥቂው ትሮሳርድ 21 ሚሊዮን ፓዎንድ የከፈለ ሲሆን በጣሊያን ሊግ የሚጫወተውን ጃኩብ ኪዊኦር በ18 ሚሊዮን አስፈርሟል።
በሚዋዥቅ አቋም ውስጥ የሚገኘው ሊቨርፑል ደግሞ ከ36-45 ሚሊዮን ፓዎንድ በሚገመት ገንዘብ የኔዘርላንድስ የፊት መስመር ተጫዋች ኮዲ ካግፖ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን አስፈርሟል።
ኒውካስትል ዩናይትድ ደግሞ የ21 ዓመቱን አንቶኒ ጎርደንን ከኤቨርተን እስከ 45 ሚሊዮን ፓዎንድ በሚደርስ ገንዝብ አዘዋውሯል።
ሊድስ ዩናይትድ ደግሞ ለፈረንሳዊው አጥቂ ጆርጂኒዩ ሩተር በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ክፍያ በመፈጸም ወደ ኢላንድ ሮድ አዘዋውሯል። ሊድስ ለ20 ዓመቱ ተጫዋች 36 ሚሊዮን ፓዎንድ ከፍሏል።













