በኮሪያ የዘመተው የአሜሪካዊው ወታደር አጽም ከ72 ዓመታት በኋላ ተገኘ

ታትሟል

በኮሪያ ጦርነት ወቅት ተገድሎ ጠፍቷል የተባለ አንድ የአሜሪካ ወታደር ከ72 ዓመታት በኋላ አጽሙ መለየቱን የአሜሪካ መንግስት አስታወቀ።

የ27 ዓመቱ ወታደር ቶሚ ቲ ሃንክስ በአውሮፓውያኑ 1950 በሰሜን ኮሪያ አንጁ ከተባለ ስፍሪያ አቅራቢያ ለመውጣት ሙከራ ሲያደርግ መገደሉ ተነግሯል። 

ከስድስት ዓመታት በኋላም አስከሬኑ “የማይገኝ” ተብሎ ተወስኖ ነበር።

በጦርነቱ ከተገደሉት መካከል ወደ 7 ሺህ 600 የሚጠጉት እስካሁን የደረሱበት አይታወቅም ሲል የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የመከላከያ  ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሃንክስ በጥቅምት 26 ከአንጁ አቅራቢያ ካለው የቾንግችኦን ወንዝ ምስራቃዊ ክፍል ለመውጣት ሲሞክር መጥፋቱ ተዘግቧል።

“አስከሬኑ ሊገኝ ካለመቻሉም በላይ የጦር ምርኮኛ ስለመሆኑም ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም” ብሏል በመግለጫው።

በኮሪያ ጦርነት ወቅት የተገደሉትን የአሜሪካ ወታደሮች አጽም የያዙ 55 ሳጥኖችን ሰሜን ኮሪያ ካስረከበች በኋላ ግን የሃንክስን ማንነት ማረጋገጥ ተችሏል።

ይህም ሊሳካ የቻለው በአውሮፓውያኑ 2018 በወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን መካከል ከተካሄደ ስብሰባ በኋላ ነው።

የሃንክስን አጽም ለመለየት ሳይንቲስቶች ከአንትሮፖሎጂካል እና ከኢሶቶፕ ትንታኔን በተጨማሪ ሁኔታዊ መረጃዎችን ተጠቅመዋል።

አስከሬኑ በአርሊንግተን ብሔራዊ መቃብር እንደሚያርፍም ተነግሯል።

ከ1982 ጀምሮ በኮሪያ ጦርነት የተገደሉ ከ450 በላይ አሜሪካውያን አጽምን በመለየት ለቤተሰቦቻቸው በማስረከብ በሙሉ ወታደራዊ ክብር እንዲቀበሩ ተደርጓል። 

ይህ ቁጥር የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ ባሉት ዓመታት ከ3 ሺህ በላይ አጽም ለአሜሪካ መልሳ አስክሬናቸው ከታወቁት 2 ሺህ አሜሪካውያን በተጨማሪ ነው።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አሁንም የደረሱበት ያልተገኙ በሚል ተመድበዋል።

የኮሪያ ጦርነት የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የተደረገው ነፍሰ በላው ግጭት ተደርጎ ይወሰዳል።

አሜሪካ ወደ 36 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮቿን አጥታበታለች።