ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሴቶች ግድያ ተጠርጥሮ በተያዘው ግለሰብ ቤት ከ200 በላይ ጦር መሳሪያዎች ተገኙ
በአሜሪካ ኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ በሦስት ሴቶች ግድያ ተጠርጥሮ ከታሰረው ግለሰብ መኖሪያ ቤት ከ200 በላይ የጦር መሳሪያዎች መገኘታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ሬክስ ሂዩርማን የተባለው የ59 ዓመቱ ግለሰብ ሜጋን ዎተርማን፣ አምበር ኮስቴሎ እና ሜሊሳ ባርቴሌሚ የተባሉ ሴቶችን ገድሏል ተብሎ በቁጥጥር ሥር ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግለሰቡ በላስ ቬጋስ የሚያስተዳድረው ንብረት አለው መባሉን ተከትሎ የላስ ቬጋስ ፖሊስ መዝገባቸው ያልተዘጋ የወንጀል ምርመራዎች ከግለሰቡ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ካለ በሚል ምርመራ ስለመጀመሩ ተዘግቧል።
ፖሊስ ከግለሰቡ መኖሪያ ቤት ካገኛቸው ከ200 እስከ 300 ከሚሆኑት ጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ አንድ ፊቷ ላይ ጉዳት የደረሰባት ሴት ፎቶግራፍም አግኝቷል ተብሏል።
የአካባቢው ፖሊስ ኮሚሽነር ሮድኒ ሐሪሰን ለፎክስ ኒውስ ሲናገሩ ግለሰቡ ጦር መሳሪያዎቹን ለብቻቸው በተለየ ክፍል ውስጥ አከማችቶ ነበር።
“ማንም ይሁን ማን እንዲህ አይነት ጦር መሳሪያ ያለው ሰው ስንመለከት ያሳስበናል” ብለዋል የፖሊስ አባሉ።
ሬክስ ሂዩርማን በመኖሪያ ቤቱ የተገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎች ምንጭ ከየት እና ለምን አገለግሎት የሚለውሉ እንደሆኑ የተባለ ነገር የለም።
የተጠርጣሪው ቤተሰብ አባላትም ይህን ያክል የጦር መሳሪያ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ስለመቀመጡ የምናውቀው ነገር የለም ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
ግለሰቡ እአአ 2010 አስክሬናቸው በአንድ ቦታ ላይ የተገኙ ሦስት ሴቶችን ገድሏል ተብሎ በቁጥጥር ሥር ቢውልም ወንጀሉን እንዳልፈጸመ ይናገራል።
መርማሪ ፖሊሶች ግን ከሦስቱ ሴቶች በተጨማሪ በሌላ አራተኛ ሴት የግድያ ወንጀል ሬክስ ሂዩርማን ላይ ክስ እንመሰርታለን እያሉ ነው።
በአራቱ ሴቶች ግድያ ፖሊስ ለዓመታት ያደረገው ምርመራ አመርቂ ውጤት ሳያስገኝ ቢቀርም፣ አሁን ግን የስልክ ምልልሶች፣ የዘረ መል ናሙና እንዲሁም ገዳዩ ሲያሸከረክር ነበር የተባለው የመኪና አይነት በቁጥጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ ላይ የሚጠቁሙ ሆነዋል።