ከሲቲ ውጭ 'ኃያላኑ' ቡድኖች ተፈትነው ኒውካስል የደመቀበት 13ኛ ሳምንት

ኒውካስትል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከማንቸስተር ሲቲ ውጭ ያሉ 'ኃያላን' ቡድኖች ነጥብ ሲጥሉ ኒውካስትል ዩናይትድ የቻምፒየንስ ሊግ ቦታን ይዟል። 

ሊቨርፑል እና ቶተንሃም በተጋጣሚዎቻቸው ሲረቱ፤ ቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና አርሰናል አቻ ተለያይተዋል። 

ቅዳሜ ዕለት ኖቲንግሃም ፎረስት በሜዳው ሊቨርፑልን አስተናግዶ ነበር። በጨዋታው ፎረስት ባስቆጠራት አንድ ጎል ሦስት ነጥቡን ጠቅልሎ ወስዷል። 

በ55ኛው ደቂቃ ነበር አዎኒይ ኳስ እና መረብ ያገናኘው። 

ሊቨርፑል አንሰራራ ሲባል ተመልሶ መውረዱን ቀጥሎበታል። 

ማንቸስተር ሲቲም በሜዳው ኢትሃድ ብራይተንን አስተናግዶ ሦስት ነጥቡን ወስዷል። 

ከሊቨርፑል ሽንፈት በኋላ ሲቲዎች ወደ ድል ለመመለስ በቅተዋል። ልማደኛው ሃላንድ ሁለት ጎሎችን ከመረብ አገናኝቷል። ቀሪዋን ጎል ደብራይን ለሰማያዊ ለባሾቹ አስቆጥሯል። 

ብራይተንን ከሽንፈት ያልታደገችውን ጎል ትሮሳርድ አስቆጥሯል። 

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ ተከናውኗል። ከጨዋታው በላይ በዲሲፕሊን ቅጣት ከዕለቱ ጨዋታ ውጭ የተደረገው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትልቁ መነጋገሪያ ነበር። 

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ምን ጎል ተጠናቋል። 

በሁለተኛው አጋማሽ ጆርጊንሆ ከፍጹም ቅጣት ምት ቼልሲን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ። መደበኛው ሰዓት ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ብራዚላዊው ካሰሚሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።  

ቅዳሜ በተካሄዱ ሌላ ጨዋታ ኤቨርተን ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል። 

እሑድ በነበረው ጨዋታ አሰልጣኙን ያሰናበተው አስቶን ቪላ ብሬንትፎርድን 4 ለ 0 አሽንፏል። 

ሊድስ ዩናይትድ ደግሞ በሜዳው በፉልሃም 3 ለ 2 ተሸንፎ ጨዋታውን አጠናቋል። 

የሳውዝሃምፕቱን ስቱዋርት አርምስትሮንግ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሳውዝሃምፕቱን ስቱዋርት አርምስትሮንግ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሊጉ መሪ አርሰናል ወደ ሳውዝሃምፕተን አቅንቶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። 

አርሰናል በ11ኛው ደቂቃ በግራኒት ዣካ ጎል ቀዳሚ መሆን ቻለ። 

መድፈኞቹ የበላይነታቸውን አስጠብቀው ይቀጥላሉ ቢባልም ሳውዝሃምፕተኖች የኋላ ኋላ ወደ ጨዋታው ተመልሰዋለው። 

ስቱዋርት አርምስትሮንግ በ65ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ሁለቱም ቡድኖች ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል። 

ሌስተር ወደ ዎልቭስ ሜዳ በማቅናት ሦስት ነጥብ ለማሳካት በቅቷል። 

ቲዬልማንስ፣ ባርነስ፣ ማዲሰን እና ቫርዲ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሌስተር 4 ለ 0 አሸንፏል።

ትላንት እሑድም ለንደን ላይ ሌላ ተጠባቂ ጨዋታ ተከናውኗል።  

ቶተንሃም ሆትስፐር በሜዳው ኒውካስልን አስተናግዷል። 

ዊልሰን እና አልሚኖር ባስቆጠሯቸው ጎሎች ኒውካስል 2 ለ 0 እየመራ የመጀመሪያውን አጋማሽ አጠናቋል። 

ከእረፍት መልስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ቶተንሃሞች በሃሪ ኬን አንድ ጎል ለማስቆጠር ቻለ። 

ቡድኖቹ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በኒውካስል የበላይነት ተጠናቀቀ። 

ጥንካሬውን ባስመሰከረበት ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን ይዞ ይወጣው ኒውካስል በደረጃ ሰንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  

የሳምንቱ የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይከናወናል። ለንደን ላይ ዌስት ሃም ከበርንማውዝ ይገናኛሉ። 

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ጨዋታውን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ዌስት ሃም እንደሚያሸንፍ ግምቱን አስቀምጧል። 

አርሴናል ሊጉን በ28 ነጥቦች በመምራት ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ እና ትላንት የተሸነፈው ቶተንሃም ሁከተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል። 

ሊድስ ዩናይትድ፣ ዎልቭስ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ደግሞ በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል። 

ኤርሊንግ ሃላንድ፣ ሃሪ ኬን እና አሌክሳንደር ሚትሮቪች የከፍተኛ ጎል አስገቢነቱን ደረጃ እየመሩ ነው። 

የማንቸስተር ሲቲው ሃላንድ በ17 ጎሎች ቀዳሚ ነው። ኬን እና ሚትሮቪች በአንድ ጎል ተበላልጠው በ10 እና በ9 ጎል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።