በደቡብ አፍሪካ በመድፈር የተከሰሰው ናይጄሪያዊ ፓስተር ከስምንት ዓመታት እስር በኋላ ነጻ ተባለ

ፓስተር ቲሞቲ ኦሞቶሶ ለመገናኛ ብዙኃን ስለተሰጠው ፍርድ እግዚአብሄርን አመስግኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፓስተር ቲሞቲ ኦሞቶሶ ስለተሰጠው ፍርድ እግዚአብሄርን እንደሚያመሰግን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ናይጄርያዊው ፓስተር በመድፈር ወንጀል ስምንት ዓመታትን በደቡብ አፍሪካ እስር ቤት ካሳለፈ በኋላ ከቀረቡበት ክሶች ሁሉ ነጻ መሆኑ ተገለፀ።

32 ክሶች ቀርበውበት የነበረው ፓስተር ቲሞቲ ኦሞቶሶ፤ ከተወነጀለባቸው ድርጊቶች ነጻ መሆኑን ለዓመታት ሲከራከር ቆይቷል።

በደቡብ አፍሪካ በመድፈር ወንጀል ተከስሶ የችሎቱ ሂደት በቀጥታ የተላለፈ የመጀመርያው ግለሰብ ሲሆን በርካታ ሰዎች ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉት ነበር።

እአአ በ2018 አንዲት ሴት ፍርድ ቤት ቀርባ ፓስተር ኦሞቶሶ በፖርት ኤልዛቤት ከተማ በሚመራው ቤተክርስትያን በ14 ዓመቷ መደፈሯን ተናግራለች።

ረቡዕ ዕለት ፍርድ ቤቱ ብይኑን ሲሰጥ ችሎቱን የሚመሩት ዳኛ፣ ፓስተር ቲሞቲ ኦሞትሶ ጥፋተኛ አይደለም ሲሉ ውሳኔውን ያነበቡ ሲሆን፣ አቃቤ ሕግ ጉዳዩን በተሳሳተ መንገድ መያዙን ገልጸዋል።

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ አቃቤ ሕግ ባለስልጣን በተከሳሹ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን፣ "በጉዳዩ ላይ የቀድሞ አቃብያነ ሕጎች አግባብ ያልሆነ ድርጊት ፈጽመዋል፤ ከሳሾቹ በመንግሥት በኩል በቂ ምርመራ አልተደረገባቸውም" ብሏል።

በቀጣይ ያሉትን "የህግ አማራጮች እንደሚያጤን" ያስታወቀው ብሔራዊው የአቃቤ ሕግ ባለስልጣን፤ ፓስተሩ በተከሰሰባቸው ጉዳዮች ላይ ብዛት ያላቸው አቤቱታዎችን ማቅረቡ የፍርድ ሂደቱ ለስምንት ዓመታት እንዲጓተት ምክንያት የሆነ አንድ ጉዳይ መሆኑን አስረድቷል።

ፓስተር ኦሞቶሶ ስለተሰጣቸው ፍርድ እግዚአብሄርን እንደሚያመሰግኑ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

ከፓስተሩ ጋር አብረውት የተከሰሱት ሉሳንዳ ሱላኒ እና ዚኪስዋ ሲቶም ከቀረበባቸው ክስ ሁሉ ነጻ መሆናቸው ተገልጿል።

ኦሞቶሶ እአአ በ2017 በቁጥጥር ስር የዋለው ደቡብ አፍሪካን ለቅቆ ሊወጣ ሲል ነው።

የፓስተር ኦሞቶሶ የፍርድ ሂደት ጾታዊ ጥቃት በተንሰራፋባት ደቡብ አፍሪካ በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ የመጀመሪያው የመድፈር ክስ ነው።

ችሎቶቹ ከፍተኛ ትኩረት የሳቡ ሲሆን በመገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ማስተላለፍ እና የቴሌቪዥን ካሜራዎችን በፍርድ ቤቶች ውስጥ ማኖር የተጎጂዎች መብትን ለመጠበቅ እና ገለልተኝነት እንዲሁም ፍትህ ለማግኘት ምን ያህል ይጠቅማል የሚሉ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የዕሮቡን ውሳኔ ተከትሎ ፓስተር ኦሞቶሶ ወደ ናይጄሪያ እንደሚባረሩ የደቡብ አፍሪካው መገናኛ ብዙሃን ኒውስ24 ዘግቧል።