የቡድን 7 አገራት የታገደ የሩሲያን ንብረትን በመጠቀም ለዩክሬን የ50 ቢሊዮን ዶላር ብድር ፈቀዱ

ዜሌንስኪ እና ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

የቡድን 7 አባል አገራት በዕግድ ላይ ያሉ የሩሲያ ንብረቶችን በመጠቀም ለዩክሬን የ50 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማቅረብ ተስማሙ።

ዩክሬን የሚቀርብላትን ብድር ከሩሲያ ጋር ለምታደርገው ጦርነት ትጠቀምበታለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህ ለሩሲያ “መቼም እንደማንመለስ” ሌላ ማስታወሻ ነው ሲሉ፤ ሞስኮ በበኩሏ “እጅግ መራር” አጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።

ዩክሬን ይህንን ገንዘብ ለመቀበል 6 ወራት ያህል መጠበቅ የግድ የሚላት ቢሆንም፣ በጦርነት የደቀቀ ኢኮኖሚያዋ እንዲያንሰራራ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል።

ከዚህ በተጨማሪ በጣልያን በተካሄደው የቡድን 7 ጉባዔ ላይ ፕሬዝዳንት ባይደን እና ዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ለ10 ዓመታት የሚዘልቅ የሁለትዮሽ የደኅነት ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን ዩክሬን “ታሪካዊ” ስትል ገልጸዋለች።

ስምምነቱ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደረገውን ወታደራዊ ትጥቅ እና የሥልጠና ድጋፍ የሚያስቀጥል ቢሆንም፣ ዋሽንግተን ወታደሮቿን ወደ ኪየቭ መላክን ግን አያካትትም።

ከሁለት ዓመት በፊት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ስትፈጽም በቡድን 7 አባል አገራት 325 በሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረቷ እንዲታገድ ተደርጓል።

ንብረቶቹ በየዓመቱ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወለድ የሚያስገኙ ናቸው።

በደቡባዊ ጣልያን በምትገኘው ፑጊላ የቡድን 7 አባል አገራት በሰጡት የጋራ መግለጫ፣ ፕሬዝዳንት ባይደን የ50 በሊዮን ዶላር ብድሩ ዩክሬን ተግባሯን እንድትቀጥል ያግዛል ካሉ በኋላ “ይህም ለሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን መቼም ወደኋላ እንደማንመለስ የሚያስታውስ ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ “ፑቲን ሊከፋፍለን አይችልም። ዩክሬን እስከምታሸንፍ ድረስ ከጎኗ እንቆማለን” ሲሉም ተደምጠዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳት ዜሌንስኪ ለአገራቸው እየተደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል። ሰምምነቱንም ታሪካዊ ሲሉ ጠርተውታል።

የበለጸጉት የቡድን 7 አባል አገራት ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ፤ ዩክሬን በሩሲያ ከተወወረችበት ጊዜ ጀምሮ በገንዘብ እና በጦር መሳሪያ ሲደግፏት ቆይተዋል።

ከዜሌንስኪ የቅርብ አማካሪዎች መካከል አንዱ ሩሲያን በዚህ መልኩ መቅጣት በጦርነቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።

ሆኖም ይህ የብድር ድጋፍ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ወዲያው እንድታቋርጥ ይረዳል ተብሎ አይታመንም። ከታገዱት የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ንብረቶች አብዛኞቹ የሚገኙት በቤልጂዬም ነው።

ዓለም አቀፍ ሕጎች አገራት የገዷቸውን የሩሲያ ንብረቶች ለዩክሬን አሳልፈው እንዲሰጡ አይፈቅድላቸውም።

ይህ ውሳኔ ይፋ ከመደረጉ በርካታ ሰዓታት ቀደም ብሎ የቡድን 7 አባል አገራት የደረሱበት ስምምነት ከሩሲያ በኩል “እጅግ መራር” አጻፋ እንደሚያስከትል የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ተናግረዋል።