7 ሺህ 200 አገልግሎት ሰጭ ዩክሬናውያን ደብዛቸው ጠፋ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ በርካታ ምስቅልቅሎች ተፈጥረዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን አድራሻቸው የጠፋውም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከእነዚህ መካከል አገልግሎት ሰጭ ዩክሬናውያን ተጠቃሽ ናቸው።
የዩክሬን እምባ ጠባቂ ተቋም እንዳስታወቀው ከሆነ ከ7 ሺህ 200 በላይ አገልግሎት ሰጭ ዩክሬናውያን የት እንደደረሱ አልታወቀም። የተቋሙ ኃላፊ ኦሌህ ኮቴንኮ እንደገለጹት አድራሻቸው ከጠፋ ዩክሬናውያን መካከል አብዛኛዎቹ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ናቸው።
ኃላፊው አክለውም ቀደም ሲል ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአገልግሎት ሰጭ ሙያተኞች መጥፋታቸውን የዩክሬን ጦር ይፋ አድርጎ እንደነበር ተናግረዋል።
እነዚህ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት የዩክሬን ዜጎች በቅርቡ ወይም ደግሞ ከጊዜ በኋላ ከሩሲያ ጋር የጦር ምርኮኞች ልውውጥ ተደርጎ እንደሚመለሱ ኃላፊው ገልጸዋል።
የእምባ ጠባቂ ተቋሙ ይህንን ይበል እንጅ የዩክሬንም ሆነ የሩሲያ ጦር በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም። ጦርነቱ ከተጀመረ ከየካቲት ወር ጀምሮ ሞስኮም ሆነች ኪዬቭ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ማርከናል እያሉ ነው።
በጦርነቱ ንጹሃን ተጎጅ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል። የሩሲያ ጦር ሰሞኑን በምስራቅ ዩክሬን ቻሲቭ ያር ከተማ በአንድ አፓርትመንት ላይ ባረፈው ሚሳኤል የሞቱት ሰዎች ቁጥር 30 መድረሱን የዩክሬን የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ተናግሯል።
በሌላኛዋ ሰሜን ምስራቃዊት የዩክሬን ከተማ ካርኪቭ በደረሰ ጥቃት ደግሞ 6 ሲሞቱ 31 መቁሰላቸው ተነግሯል።
ጦርነቱ በተለያዩ አቅታጫዎች ቢቀጥልም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬናውያን የሩሲያን ዜግነት በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችለውን ድንጋጌ ፈርመዋል።
እሁድ ዕለት የዩክሬኑ የመከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦርን ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ 1 ሚሊዮን ጠንካራ ጦር በማዘጋጀት ደቡባዊ የዩክሬን ግዛትን እናስመልሳለን ብለዋል።
በጥቁር ባሕር ዳርቻ ያሉትን አካባቢዎች መልሶ መቆጣጠሩ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማነቃቃት ከፍተኛ ሚና ነበረው ብለዋል ሚንስትሩ።
ተንታኞች እንደሚሉት ግን ይህ እንዲሁ በስሜት የተነገረ እንጅ በተግባር የታቀደ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ላይሆን ይችላል።












