አንድ ባለጸጋ የዩኬ ቤተሰብ “አያቶቻችን ባሪያ አሳዳሪ ስለነበሩ ይቅርታ እንጠይቃለን” አለ

አንድ የዩኬ ሃብታም ቤተሰብ አያት፣ ቅድመ አያቶቻችን ባሪያ ፈንጋይና ባሪያ አሳዳሪ ስለነበሩ ይቅርታ በይፋ እንጠይቃለን አሉ።
በካሪቢያን የግሬናዳ ደሴት ባሪያዎችን በሰፋፊ እርሻዎች በማሠራት ቅድመ አያቶቻችን ለፈጸሙት ጥቃት ወደ ደሴቲቱ ሄደን በይፋ ይቅርታ እንጠይቃለን ያለው ይህ ባለጸጋ ቤተሰብ ትሬቬሌያን በሚል ስም ይታወቃል።
በዚህ ደሴት ብቻ በ19ኛው ክፍለ ዘመን 6 ሰፋፊ የሱኳር እርሻዎች የነበሩት የባላባት ቤተሰብ ነው።
የዚህ ቤተሰብ አባል የሆነችውና አሁን የቢቢሲ ዘጋቢ ሆና የምትሠራው ላውራ ትሬቬሌያን ከወራት በፊት የግሬናዳ ደሴትን ጎብኝታ ነበር።
ላውራ እዚያ በተመለከተችው ነገር ፍጹም እንዳዘነች ተናግራለች። እንደ አውሮጳዊያኑ 1833 ላይ የባሪያ ፍንገላ ሲቆም ደግሞ ቅድመ አያቶቿ በዩኬ መንግሥት ካሳ እንዲያገኙ መደረጉ ይበልጥ እንዳስደነገጣት ተናግራለች።
ያን ጊዜ ባለጸጋ ቤተሰቦቿ ከፍተኛ ገንዘብ በካሳ መልክ ቢያገኙም ባሪያዎች ግን ሽራፊ ሳንቲም አልተሰጣቸውም።
ይህ ባለጸጋ ቤተሰብ በደሴቲቱ አንድ ሺህ የሚሆኑ ባሪያዎችን ያስተዳድር ነበር።
ትናንት ቅዳሜ ለቢቢሲ በግል ሐሳቧን ያጋራችው ባልደረባችን ላውራ ወደ ደሴቲቱ ዘጋቢ ፊልም ለመሥራት ተጉዛ ባየችው ነገር ልቧ መሰበሩን አብራርታለች።
“በቃ ብቻ አስቀያሚ ነገር ነው የሆነው፤ እነዚያን የአገዳ እርሻዎችን ተመለከትኳቸው። ባሪያዎች ይገረፉባቸው የነበሩትን ክፍሎች አየሁ። ባሪያዎች የሚታሰሩባቸውን ሰንሰለቶች ተመለከትኩ፤ ባየሁት ነገር ሁሉ አፍሪያለሁ” ብላለች።
ላውራ በነገሩ ማዘን ብቻ በቂ እንዳልሆነ እንደተሰማት ለቢቢሲ አስረድታለች።
“ታሪክን መጠገን አይቻልም፤ ለደረሰ ግፍና በደል ግን እውቅና መስጠት ያስፈልጋል” ብላለች።
የቢቢሲዋ ላውራ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ሰባት የቤተሰቧ አባላት ወደ ካሪቢያን ደሴት በያዝነው ወር ተጉዘው በይፋ ይቅርታ ይጠይቃሉ ብላለች።
ይህ ብቻ ሳይሆን 120ሺህ ዶላር በማውጣት አካባቢውን በኢኮኖሚ የሚደግፍ በጎ አድራጎት ሥራም ይጀምራል ብላለች።
ላውራ እንዳለችው እንደ አውሮፓዊያኑ በ1834 ቅድመ አያቶቿ 34ሺህ ፓውንድ በካሳ መልክ አግኝተው ነበር። አሁን ይህ ገንዘብ 3 ሚሊዮን ፓውንድ ይገመታል።
“ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ 100ሺህ ፓውንድ መክፈል በቂ ነው ብዬ በግሌ አላምንም። ይሁንና ምሳሌ መሆንና ለተሠራው ጥፋት በይፋ መጸጸታችንን ለማሳየት ይሆን ይሆናል” ብላለች።
የግሬናዳ ብሔራዊ የመልሶ ማልማት ኮሚሽን የዚህን ባለጸጋ የዩኬ ባሪያ አሳዳሪ ቤተሰብ ተግባር በበጎ እመለከተዋለሁ ብሏል።
የዚህ ባለጸጋ ቤተሰብ አባል የሆነችውና አሁን በኒው ዮርክ የቢቢሲ ዘጋቢ ሆና የምታገለግለው ላውራ ወደ ግሬናዳ ደሴት የሄደችው “ብላክ ላይቭስ ማተር” እንቅስቃሴ በተፋፋመበት ወቅት ነበር።
በርካታ የምዕራብ አገራት ቤተሰቦች በካሪቢያን እና አፍሪካ ውስጥ ሰፋፊ እርሻዎችን በመያዝ ባሪያዎችን በግፍ ጉልበታቸውን በመበዝበዝ ስፍር ቁጥር የሌለው ሃብት ንብረት አፍርተዋል።












