የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ የኪዬቭ ነዋሪዎች ውሃ ለማግኘት ተሰለፉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሰኞ ዕለት ሩሲያ በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ የዩክሬን ዋና መዲና ኪዬቭ ነዋሪዎች ውሃ ለማግኘት ተሰልፈዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊይ ክሊሽኮ እንዳሉት በኪዬቭ የሚኖሩ 40 በመቶ የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ውሃ የሌላቸው ሲሆን 270 ሺህ የሚሆኑ ቤቶችም የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል።
በተፈፀመው ጥቃት በመላ አገሪቷ አስራ ሦስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ዩክሬን ገልጻለች።
ሩሲያ በበኩሏ የጥቃቱ ኢላማ የዩክሬን ጦር መቆጣጠሪያ እና የኃይል ሥርዓቱ መሆኑን ገልጻ፣ ሁሉንም ኢላማዎቿን መምታቷን አስታውቃለች።
ይህም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በሩሲያ የጦር መርከብ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ መሆኑን የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ ከተተኮሱበት 55 ሚሳይሎች 45ቱን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።
ለደኅነንት ሲባል የውጩ ዓለም በሩሲያ ጥቃት የፈራረሱ የዩክሬን ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን እምብዛም አያሳዩም።
ይህ የሆነው ጥቃት የደረሰባቸውንና ያልደረሰባቸውን ቦታዎች ጨምሮ ወደፊት ለሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊጠቅሙ ይችላሉ የተባሉ መረጃዎችን አሳልፎ ላለመስጠት መሆኑን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ሰኞ ዕለት የተፈፀመው ጥቃት ተፅዕኖ ሁሉም ቦታ እየታየ ነው። በበርካታ ክልሎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጧል።
በአጠቃላይ የዩክሬን ዜጎች የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አሳስበዋል።
ነዋሪዎች የሚያገኙት የውሃ አገልግሎት ከተቋረጠባቸው በኋላም ከፓምፕ ውሃ ለመቅዳት ረጃጅም ወረፋዎች ታይተዋል።
80 በመቶ የሚሆኑት የኪዬቭ ነዋሪዎች ከጥቃቱ በኋላ ምንም ውሃ እንደሌላቸው ተገልጿል።
ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ አገልግሎቶቹን ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
“ሩሲያ የዩክሬን ዜጎችን የመኖር ፍላጎት የሚያጠፋ ሚሳይል የላትም” ሲሉም ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።
ከዋና መዲናዋ በተጨማሪም ሊቪቭ፣ ዲኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ካርኪቭ እና ዛፖሪዢያን ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችም ለተመሳሳይ ችግር ተዳርገዋል።
በአጠቃላይ በአስር ክልሎች በተፈፀመ የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት 18 መሠረተ ልማቶች መመታታቸውንና ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የኃይል ማመንጫ መሆናቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ኢላማው ቦታ ሳይደርስ በዩክሬን አየር ኃይል ተመትቶ የወደቀው አንደኛው ሚሳኤል በድንበር ከተማዋ ሞልዶቫ የወደቀ ሲሆን ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።
ይሁን እንጂ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የጎረቤት አገር ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
በኋላ ላይ ግን በቺሲናው የሚገኙ የሩሲያ ኤምባሲ ሠራተኛ ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸው እንደነበር ሞልዶቫ ገልጻለች።
የሰኞ ዕለቱ ጥቃት የተፈፀመው ሩሲያ በጠቀለለቻት የክሬሚያ የባህር ሰርጥ ጥቁር ባህር ላይ በነበሩ የጦር መርከቦች ላይ የድሮን ጥቃት ፈፅማለች ስትል ከከሰሰች በኋላ ነው። ይሁን እንጂ ኪዬቭ በክሱ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።
ፕሬዚደንት ፑቲን ሰኞ ዕለት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ጥቃቱ ለተፈፀመባት ጥቃት ከፊል አጸፋዊ ምላሽ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ አክለውም ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት አሸማጋይነት የተደረገውንና ከዩክሬን ወደቦች እህል የጫኑ መርከቦች በሰላም እንዲያልፉ ከሚፈቅደው ስምምነት ብትታገድም ተሳትፏዋን ግን አላቋረጠችም ብለዋል።
ሆኖም ዩክሬን ምንም እንኳን ሩሲያ ከስምምነቱ ብትወጣም መርከቦች ከወደቡ መነሳታቸውን ቀጥለዋል ብላለች።
በቅርቡ የተፈፀሙ ጥቃቶች ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈፅመው ጥቃት፣ የሙቀት መጠኑ ከኔጋቲቭ 20 ድግሪ ሴልሺየስ በታች ከሚሆንበት የክረምት ወቅት ቀደም ብሎ መሠረተ ልማቶችን ማውደም በዩክሬን ላይ የሚኖራት የጦር ስትራቴጂ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ዩክሬን በበኩሏ ጦሯ በፈፀመው መልሶ ማጥቃት ግዛቶችን መመለስ በመቻሉ ሩሲያ የምትፈፅመው ጥቃት ለጦሯ መሸነፍ የምትሰጠው ምላሽ ነው ብላለች።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭ፣ የሩሲያን ዘመቻ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በዩክሬን አዲስ ኮማንደር ሆነው በፕሬዚደንት ፑቲን ከተሾሙት ጀኔራል ሰርጌ ሱሮቪኪን ንግግር ጋር አያይዘውታል።
ባለፈው ሳምንት በተደረገውና ብዙም ባልተለመደው መግለጫ ሚኒስትሩ፣ በቅጽል ስማቸው ጀኔራል አርባጌዶን በመባል የሚታወቁት ጀኔራል ሱሮቪኪን ከተሾሙ በኋላ የሩሲያ ኃይሎች "ስልታቸውን ለውጠዋል" ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም “ ከዩክሬን ጦር ጋር ሳይሆን ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩበት ቦታ ውጊያ ተጀምሯል” ብለዋል።
"የዚህ ዓላማም በጣም ቀዝቃዛ እና ጨለማ ሲሆን በሕዝቡ ዘንድ ድንጋጤን እና ትርምስ ለመፍጠር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ ይህንን ስልት "ሽብርተኝነት" ብለውታል። በርካታ ዩክሬናውያን በበኩላቸው ምንም እንኳን ሰላማዊ ሰዎች የሩሲያ ኢላማ በመሆናቸው ቢያስቆጣቸውም እንደማይፈሩ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊየንን ጨምሮ ምዕራባውያን መሪዎችም ሆን ተብሎ በሰላማዊ ሰዎች መገልገያ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈፀም የጦር ወንጀል እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም ሞስኮ ምንም የጦር ወንጀል የሚሆን ድርጊት አልፈፀምኩም ብላለች።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚይትሮ ኩሌባም “ ሩሲያ በጦር ሜዳ ከመዋጋት ይልቅ ከሲቪሎች ጋር ትዋጋለች” ሲሉ የበርካታ ወገኖቻቸውን አስተያየት አስተጋብተዋል።
ዩክሬን ከተሞቿን ለመከላከል ተጨማሪ የአየር መከላከያ አቅም እንደሚያስፈልጋት ገልጻለች።
ጀርመን የጦር መሣሪያ የላከች ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካም መሣሪያ እንደሚልኩ አስታውቀዋል።












