ተከዜ ወንዝ ላይ በደረሰ የጀልባ አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ተከዜ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሰሃላ ሰየምት ወረዳ ተነስታ በተከዜ ወንዝ ላይ ስትጓዙ በነበረች ጀልባ ላይ በደረሰ የመስመጥ አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ።

በወረዳው ወደ ዝቋላ በተከዜ ወንዝ ላይ በጀልባ ሲጓዙ የነበሩት ሰዎች ምክንያቱ ያልታወቀ አደጋ ደርሶባቸው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ ያለ እንደሆነ ሌሎች እየዘገቡ ቢሆንም ክልሉ 12 መሆናቸውን አመልክቷል።

አደጋው የደረሰው ቅዳሜ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም. እኩለ ቀን ገደማ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ጀልባዋ 26 ሰዎችን በማሳፈር ስትጓዝ ነው።

ከአደጋው በኋላ 14 ሰዎች በሕይወት ቢተርፉም ቀሪዎቹ 12 ሰዎች ግን በወንዙ ውስጥ ሰምጠው ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል። እስከ እሁድ ጠዋት ድረስም ከወንዙ ውስጥ ማውጣት የተቻለው አስከሬን የተወሰኑትን ብቻ ሳይሆን ቀሪዎቹን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደነበር ተዘግቧል።

አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች ከእንጨት በተሠራው ጀልባ አማካይነት የተከዜ ወንዝን አቋርጠው ዝቋላ በሚባል አካባቢ በሚካሄድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በመጓዝ ላይ ሳሉ እንደነበረ ተገልጿል።

ጀልባዋ እንድትገለበጥ ምክንያት የሆነው በወንዙ ላይ በተፈጠረ ደራሽ ጎርፍ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ከተሳፋሪዎቹ መካከል የነበረ አንድ ሕጻንን ጨምሮ በአደጋው ምክንያት "ከባድ የመቁሰል አደጋ" ደርሶባቸው በሕይወት የተረፉት ሰዎች ለህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የክልልኡ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉት ሰዎች አስከሬን ሙሉ በሙሉ ከውሃው ያልጣ ሲሆን፣ ፍለጋው እየተካሄደ መሆኑን የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ተናግረዋል።

ከአገልግሎት ውጪ የሆነው የተከዜ ወንዝ ድልድይ ባለፈው ወር ሊጠናቀቅ የነበረ ቢሆንም መዘግየቱን የአካባቢው ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙኃኑ ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎችን በሚያቋርጠው የተከዜ ወንዝ ወንዝ አቅራቢያ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ወንዙን ለመሻገር ባሕላዊ ጀልባዎችን ይጠቀማሉ።

አሁን በአደጋው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በወንዙ ላይ ከዚህ በፊት ባጋጠሙ አደጋዎች ከፍተኛ ሞት ካጋጠመባቸው መካከል የሚጠቅስ ነው።