የትናንቱ ደርቢ ማንችስተርን ‘ቀይ’ አስብሏል፤ የሰሜን ለንደን ደርቢ ውጤትስ ምን ሊሆን ይችላል?

ታትሟል

ትናንት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የአንድ ከተማ ባላንጣዎቹ በማንችስተር ደርቢ ተፋጠው ነበር።

ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ።

ኦልትራፎርድ ላይ በነበረው ጨዋታ የማንችስተር ደርቢ አሸናፊነት ግምት የተሰጠው ለሰማያዊዎቹ ሲቲዎች ነበር።

ሲቲዎች ከሳምንታት በፊት ዩናይትድን በሜዳቸው ሲያስተናግዱ 4 ጎሎችን አከታትለው አስቆጥረው ዩናይትድን 6 ለ 3 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለው ነበር።

ማንችስተር 6 ተቆጥሮበት በሲቲ ሲሸነፍ ገና ከብራይተን እና ብሬንትፎርዱ አስደንጋጭ ሽንፈት አላገገመም ነበር።

አሁን ላይ ኤሪክ ቴን ሃግ እየመሩት ያሉት ማንችስተር ዩናይትድ የተለየ ሆኗል። ቀድሞ የተሰጡት ግምቶችን በመቀልበስ ዩናይትድ በሜዳው እና በደጋፊው ታጅቦ ሲቲን 2 ለ1 በመርታት ማንችስተር ከተማ የቀያይ ሰይጣኖቹ ‘ቀይ’ ነው አስብለዋል።

ዩናይትድ በዚህ የውድድር ዓመት በሜዳው አርሰናልን፣ ሊቨርፑል እና ቶተነሃምን አሸንፏል። ትናንት በሻምፒዮኖቹ ላይ ያስመዘገቡት ጣፋጭ ድል ግን ለቀሪው የውድድር ዓመት በቡድኑ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።

ሰማያዊዎቹ ሲቲዎች በዩናይትድ በመሸነፍ ከመሪው አርሰናል ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በትናንቱ ጨዋታ ቀድሞ ጎልን ከመረብ ማገናኘት የቻለው እንግዳው ቡድን ሲቲ ነበር።ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጃክ ግሪሊሽ ከኬቪን ደብረዊያን የተሻገረለንትን ኳስ በጭንቅላት አስቆጠረ።በዚህም የሲቲ የማሸነፍ ዕድልን ከፍ አደረገ።

ቀያዮቹ ከ20 ደቂቃ ገደማ በኋላ ምላሽ ሰጡ። አምበሉ ብሮኖ ፈርናንዴዝ ቡድኑን አቻ አደረገ። ብሮኖ ግቡን ያስቆጠረው ከጨዋታ ውጪ የነበረውን ራሽፎርድን ከለላ አድርጎ ስለነበረ የጎሏ መጽደቅ ሲቲዎችን ያበሳጨች ሆናለች።

ቀጠል አድርጎ አስደናቂ አቋም ላይ የሚገኘው ራሽፎርድ ሁለተኛዋን ጎል አስቆጥሮ ቡድኑ ወሳኝ ሦስት ነጥብን ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።

ራሽፎርድ ትናንት ቡድኑን አሸናፊ ያደረገችውን ጎል ጨምሮ ባለፉት 7 ተከታታይ ጨዋታቸው 8 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

አርሰናል ዛሬ ከቶተነሃም የሚያደርገው ጨዋታ እየቀረው ሊጉን በ44 ነጥብ እየመራ ይገኛል።ሲቲ ደግሞ በ39 ሲከተል፤ ዩናይትድ ከሲቲ በ1 ብቻ ተበልጦ በ38 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሰሜን ለንደን ደርቢ

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በባላንጣነት ከሚተያዩ የአንድ ከተማ ክለቦች ቀዳሚዎቹ አርሰናል እና ቶተነሃም ናቸው ቢባል ማጋነን ላይሆን ይችላል።

ሁለቱ የሰሜን ለንደን ክለቦች የሚገናኙት በወሳኝ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነው።

አርሰናል ይህን ጨዋታ አሸንፎ እግር በእግር እየተከተሉት ካሉት ሲቲ እና ዩናይትድ ልዩነቱን የሚያሰፋበት ዕድልም ከመሆኑ በላይ በደርሶ መልስ ጨዋታ ቶተነሃምን የሚረታበት አጋጣሚ ይሰጠዋል።

ቀደም ሲል በኢሚሬትስ በነበረው የሰሜን ለንደርን ደርቢ አርሰናል ቶተነሃምን 3ለ1 አሸንፎ ነበር።

5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተነሃም በሜዳው በአርሰናልን ላለመረታት ከመጫወቱም በላይ ወሳኟን ሦስት ነጥብ በመሰብሰብ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድልን ይፈጥራል።

የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ይህን ጨዋታ አርሰናል 3 ለ 0 ያሸንፋል የሚል ግምት ሰጥቷል።

አርሰናል ባለፉት 11 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፉም። በእርግጥ በዚህ የውድድር ዘመን መድፈኞቹ 1 ግዜ በማንችስተር ሲሸነፉ ሁለት ግዜ አቻ ተለያይተዋል።

በአንጻሩ ቶተነሃም ባለፉት 11 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 5 ግዜ ተሸንፈዋል።

ሱቶን አርሰናል የተሻለ ቡድን ነው፤ የቶተነሃም አጨዋወት ደግሞ ከሚጠበቀው በታች ነው ይላል።