ሩሲያ በአንድ ጥቃት ከ600 በላይ የዩክሬን ወታደሮችን ገደልኩ አለች

ታትሟል

ሞስኮ በሚሳኤል የጅምላ ጥቃት ከ600 በላይ የዩክሬን ወታደሮችን ገደልኩ አለች።

የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ካራማቶራስክ በተባለች ከተማ የወታደሮች መኖሪያ ሕንጻ ላይ የሚሳኤል ጥቃት አድርጌ 600 ወታደሮች ሲገደሉ ከ1ሺህ 300 በላይ ወታደሮችን ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።

ዩክሬን በበኩሏ ጉዳዩን ፕሮፖጋንዳ ነው ስትል አስተባብላለች።

ሞስኮ ይህን ጥቃት ስለማድረሷ ምንም አይነት ማስረጃ ሳታቀርብ፤ ይህን እርምጃ የወሰድኩት ከቀናት በፊት በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ዕለት ለተገደሉት ወታደሮቼ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ነው ብላለች።

በአውሮፓውያኑ 2023 አዲስ ዓመት ቀን በዩክሬን የሚሳኤል ጥቃት 89 ወታደሮቿ መገደላቸውን ሞስኮ ይፋ አድርጋ ነበር።

ዩክሬን በበኩሏ ዶኔስክ ግዛት ውስጥ ባለ የምልምል ወታደሮች ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ ባደረስኩት ጥቃት የሞቱት 400፤ የቆሰሉት ደግሞ 300 ናቸው ብላ ነበር።

ከዩክሬን ጥቃት በኋላ የሩሲያ ጦር ጠላት የወታደሮቹን መገኛ መለየት የቻለው ወታደሮቹ የተከለከለ ሞባይል ስልክ እየተጠቀሙ ስለነበረ ነው ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

ሩሲያ ለዚህ ጥቃት አጸፋዊ እርምጃ ወስጃለሁ ማለቷን ግን ዩክሬን ሐሰት ነው ብላለች።

የዩክሬን ጦር ቃል አቀባይ ሴርሂይ ቼሬቫትይ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ “ይህ የሩሲያ ፕሮፖጋንዳ አንዱ አካል ነው” ብለዋል።

ሞስኮ አድርሻለሁ ላለችው ጥቃት ዝርዝር ማረጋገጫ እስካሁን ባትሰጥም የሩሲያ ባለስልጣናት ጥቃቱን ያሳያል ያሉትን ምስሎች ቢቢሲ ከሳተላይ ምስሎች ጋር ሲያመሳክር ምስሎቹ ጥቃት ተፈጽሞበታል በተባለው ከራማቶርስክ ከተማ እንደተወሰዱ አረጋግጧል።

ሞስኮ በከራማቶርስክ ከተማ አድርሻለሁ ካለችው የሚሳኤል ጥቃት በተጨማሪ በሌሎች የዩክሬን ከተሞች የሚሳኤል ድብደባዎች ስትፈጽም ነበር።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ36 ሰዓታት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለወታደሮቻቸው ትዕዛዝ ቢሰጡም ሞስኮ የራሷን የተኩስ አቁም ትዕዛዝ አለማክበሯን መረጃዎች ያሳያሉ።

ባለፉት ሰዓታት በዩክሬን ደቡባዊ ከተሞች ዛፖሬዢያ እና ሜሊቶፖል ከተሞች የፍንዳታ ድምጽ ሲሰማ ነበር።

በተያያዘ ዜና የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር በዩክሬን ተማርከው የነበሩ 50 ወታደሮቹን በድርድር ማስመለሱን ገልጿል።

ዩክሬን ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ወታደሮቿን በድርድሩ ማስመለሷን በመግለጽ የምርኮኛ ልውውጥ መደረጉን አረጋግጣለች።