ከግድያ ወንጀል ነጻ መሆኑ አወዛግቦ የነበረው ኦጄ ሲምፐሰን በ76 ዓመቱ አረፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞ የአሜሪካ እግር ኳስ ኮከብ እና ተዋናይ የነበረው እና በሁለት ግድያዎች ወንጀል ክስ ነጻ መሆኑ አወዛጋቢ የነበረው ኦጄ ሲምፕሰን በ76 ዓመቱ አረፈ።
ሳንፍራንሲስኮ የተወለደው ኦሬንታል ጄምስ ሲምፐሰን (ኦጄ ሲምፕሰን) የአሜሪካን ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ኤንኤፍኤልን) ከመቀላቀሉ በፊት በኮሌጅ ቆይታው ዝነኛ ለመሆን በቃ።
የቀድሞ ባለቤቱን ኒኮል ብራውን እና ጓደኛዋን በመግደል ወንጀል ተከሶ የነበረው ኦጄ ሲምፕሰን በአውሮፓውያኑ 1995 ነጻ ነው ተባለ።
የፍርድ ሂደቱም የአሜሪካውያንን ጨምሮ የበርካቶችን ቀልብ ይዞ የነበረ ሲሆን የነጻ ብያኔውም ከፍተኛ ውዝግብን ፈጥሯል።
በአውሮፓውያኑ 2008 በጦር መሳሪያ ዘረፋ ወንጀል ክስ የ33 ዓመት እስራት የተፈረደበት ሲሆን በ2017 ተለቋል።
በፕሮስቴት ካንሰር ህመም ምክንያት የኬሞ ቴራፒ ህክምና ላይ እንደነበርም ፕሮ ፉትቦል ሆል ኦፍ ፌም በመግለጫው አስታውቋል።
ቤተሰቦቹ እንዳሉት ኦጄ በልጆቹ እና የልጅ ልጆቹም ተከቦ ነው ህይወቱ ያለፈው።
ኦጄ የቀድሞ ባለቤቱን ኒኮል ብራውን እና ጓደኛዋን ሮን ጎልድማንን በመግደል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው በአውሮፓውያኑ 1994 ነበር።
ጥንዶቹ በሎስ አንጀለስ ከሚገኘው የኒኮል መኖሪያ ቤት ውጭ በስለት ተወግተው ነው ተገድለው የተገኙትት። ኦጄም ተጠርጣሪ ሆነ።
እጁን መስጠት በነበረበት ወቅት ከቀድሞ የቡድን ጓደኛው ጋር ነጭ ፎርድ ብሮንኮ በተሰኘው መኪና የሸሹ ሲሆን ፖሊስም በሎስ አንጀለስም ሲያሳድዳቸውም ነበር ተብሏል። የፖሊስም ማሳደድ በአሜሪካ የሚገኙ የዜና ቻናሎች በቀጥታ ተላልፏል።
በአሜሪካ ሚዲያዎች “የክፍለ ዘመኑ የፍርድ ሂደት” ተብሎ በተሰየመው ክስ አቃብያነ ህግ ኦጄ ኒኮልን የገደላት በቅናት ነው የሚል መከራከሪያም አቅርበው ነበር። እንደ ማስረጃም ደም፣ ጸጉር እና ሌሎች ነገሮችም ቀርበው ነበር።
የኦጄ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ በዘረኝነት ምክንያት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው ሲሉ በመከላከያቸው አቅርበዋል።
በፍርድ ሂደቱ ከሚታወሱ ጉዳዮች መካከል ግድያው በተፈጸመበት ቦታ ተገኝተዋል የተባሉ በደም የተጨማለቁ ጓንቶችን አቃብያነ ህግ ኦጄን እንዲያጠልቀው መጠየቃቸው ነው። ጓንቶቹ ልክ ሊሆኑት አለመቻሉም ለጠበቆቹ መከላከያ ጠቅሟል ተብሏል።












