የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ፡ ማንቸስተር ሲቲ እና ሪያል ማድሪድ ወደ ቀጣዩ ዙር ተሻገሩ

ታትሟል

በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ እና የስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግረዋል።

ሲቲ ተቀናቃኙ ኮፐንሀገንን 3-1 በማሸነፍ በፍፁም የበላይነት ሩብ ፍፃሜውን ሲቀላቀል ኧርሊንግ ሃላንድ አንድ ጎል አስቆጥሯል።

ከሶስት ሳምንት በፊት ኮፐንሀገን በተደረገው ፍልሚያ ሲቲ ከሜዳው ውጭ በተመሳሳይ 3-1 አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል።

ኮፐንሀገን ምናልባት ውጤቱን ይቀለብሰው ይሆን ወይ? የሚለው ጥያቄ በአጭሩ የተቀጨው በዘጠኝ ደቂቃ ውስጥ አካንጂ እና አልቫሬዝ ለሲቲ ሁለት ጎሎች ካስቆጠሩ በኋለ ነው።

ስድስተኛ የቻምፒዮንስ ሊግ ጎሉን ያስቆጠረው የሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ ከባየር ሚዩኒኩ ሃሪ ኬን እና ከፓሪ ሳን ዠርማው ኪሊያን ምባፔ እኩል ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን ይመራል።

ኖርዌያዊው አጥቂ በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል በማስቆጠር ለሲቲ ስኬት ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረጉን ቀጥሏል።

ማንቸስተር ሲቲ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በሚቀጥለው እሑድ ከሊቨርፑል ጋር ወሳኝ ፍልሚያ ይጠብቀዋል።

ሲቲ በሰባት ተከታታይ የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ለሩብ ፍፃሜ መድረስ ችሏል።

ከዚህ ቀደም ለስምንት ተከታታይ ዓመታት በአውሮፓው ቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ መጫወት የቻለው ብቸኛው የእንግሊዝ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ ነበር።

ፔፕ ጉዋርዲዮላ ቀጣይ እሑድ የሚጠብቀን የሊቨርፑል ጨዋታ አሁን አያሳስበኝም ሲሉ ከረቡዕ ጨዋታ በፊት አስተያየት ሰጥተዋል።

ነገር ግን ከኮፐንሀገን ጋር በነበረው ጨዋታ በርካታ ተጫዋቾችን ቀይረው ማሰለፋቸው ይህን አስተያየታቸውን ውድቅ አድርጎታል።

ሀላንድ፣ ሮድሪ፣ ሩበን ዲያዝ እና ሌሎች ተጫዋቾች ተቀይረው ሲወጡ የተመለከ ፔፕ ለእሑዱ ጨዋታ እያሴሩ እንደሆነ መገመት አያዳግተውም።

በሌላ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በሜዳው አርቢ ሊፕዚግን ያስተናገደው የስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ በአቻ ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግሯል።

በመጀመሪያው ዙር ፍልሚያ 1 ለምንም የረታው ሪያል ማድሪድ በቪኒሲየስ ጁኒዬር ጎል ተንጠልጥሎ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል።

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የዙር 16 ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንትም የሚቀጥሉ ሲሆን አርሰናል ከፖርቶ የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።

በመጀመሪያው ጨዋታ በፖርቶ ሜዳ ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል በሜዳው ይህን ለመቀልበስ ይጫወታል።

ባርሴሎና ከናፖሊ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከኢንተር ሚላን፤ ቦሩሲያ ዶርትመንድ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን ሌሎች ቀጣይ ሳምንት የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።

ሲቲ፣ ማድሪድ፣ ፓሪ ሳን ዠርማ እና ባየር ሚዩኒክ ደግሞ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው።