ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል? ሲቲ፣ ሊቨርፑል ወይስ አርሰናል? ትንበያዎች ምን ይላሉ?
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በዓመታት ውስጥ ጠንካራ የዋንጫ ፍክክር የታየበት ዓመት ያለንበት የውድድር ዘመን ነው።
ሊቨርፑል ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር በነበረው ጨዋታ በተጨማሪ ሰዓት መጠናቀቂያ ላይ ያስቆጠራት ግብ መሪነቱን እንዲያስጠብቅ አስችላዋለች።
እሑድ ዕለት በኢቲሃድ ማንችስተር ዩናይትድን ያስተናገደው ማንችስተር ሲቲ ደግሞ ከመመራት ተነስቶ 3 -1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት በድጋሚ በአንድ ነጥብ ማጥበብ ችሏል።
ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ዛሬ [ሰኞ] ምሽት ከሜዳው ውጪ ወራጅ ቀጠና የሚገኘውን ሼፊልድ ዩናይትድን ይገጥማል።
አሁን ባለው የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ሊቨርፑል በ27 ጨዋታ 63 ነጥቦችን በመሰብሰብ በ39 ተጨማሪ የግብ ክፍያ አንደ ኛደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ማንችስተር ሲቲ በተመሳሳይ የጨዋታ ብዛት 62 ነጥቦችን ሰብስቦ በ36 የግብ ክፍያ ይከተላል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው አርሰናል፣ በ26 ጨዋታዎች 58 ነጥብ በመሰብሰብ እና 39 የግብ ክፍያዎችን በመያዝ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የፔፕ ጉዋርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ ከተፎካካሪዎቹ አንጻር ሲታይ በቀጣዮቹ ሳምንታት በተለየ ከባድ ጨዋታዎች ይጠብቁታል።
በእነዚህ ሳምንታት ማንችስተር ሲቲ ሁለቱንም ተፎካካሪዎቹን የሚገጥም ይሆናል።
ሲቲ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወደ አንፊልድ ተጉዞ ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ይፋለማል። በመጋቢት ወር መገባደጃ ላይ ደግሞ በሜዳው አርሰናልን ያስተናግዳል።
ሊቨርፑል በ19 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች የተሸነፈው በአርሰናል ብቻ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ማንችስተር ሲቲን ካስተናገደ በኋላ ሊቨርፑሎች ቀጣይ በሜርሲሳይድ ደርቢ ወደ ጉዲሰን ፓርክ ተጉዘው ከኤቨርተን ጋር ይፋለማሉ።
የትንበያ ሞዴሉ ምን ይላል?
በኦፕታ ትንበያ መሠረት ማንችስተር ሲቲ የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከፍ ያለ ግምት ተሰጥቶታል።
ያለፈው ዓመት ባለድል ማንችስተር ሲቲ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የማንሳት ዕድሉ 52.9 በመቶ መሆኑን ኦፕታ ተንብይዋል።
ሊቨርፑል በ35.9 በመቶ ሁለተኛ ዕድል አለው ያለው ኦፕታ፣ አርሰናል ደግሞ ዋንጫ የማንሳት ዕድሉ 11.2 በመቶ ነው ብሏል።
ኦፕታ ይህንን ግምት የሚሰጠው የቀጣዮቹን ጨዋታዎች ሁኔታ፣ የስፖርት ውርርድ ገበያ ግምቶችን እና የኦፕታ ቡድን ግምገማዎችን ከክለቦች ወቅታዊ አቋም ጋር በማመዛዘን ነው።
ይህንን ትንበያ ለመሥራት በሺዎች ለሚቆጠር ጊዜ ሙከራ ተደርጓል።
ያም ቢሆን ግን የፕሪሚዬር ሊጉ ፍጻሜ እስከሚደረግበት ግንቦት 11 ድረስ በርካታ የደረጃ መፋለሶች ሊኖሩ ይችላሉ።