ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፌስቡክ ባለቤት ሜታ 10 ሺህ ሠራተኞችን ሊቀንስ ነው
ፌስቡክ፣ ኢንስታግራምና ዋትስአፕን በባለቤትነት የያዘው ሜታ 10 ሺህ ሰራተኞችን የመቀነስ እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይም 11 ሺህ ሰራተኞችን የቀነሰ ሲሆን አሁን ይደረጋል የተባለው ቅነሳ ኩባንያው በርካታ ሰራተኞችን የመቀነስ እቅዱ ሁለተኛ ዙር ነው።
የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ቅነሳው የዓመቱ ውጤታማነት አካለው ነው ያሉ ሲሆን ውሳኔው ግን ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል።
10 ሺህ ሠራተኞችን ከመቀነስ በተጨማሪ በኩባንያው ያሉ 5 ሺህ ክፍት የስራ መደቦች ላይ ቅጥር እንደማይፈጸም ጨምረው ጠቅሰዋል።
ዙከርበርግ ለሠራተኞቹ በላኩት መልዕክት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ያልተጠበቀ የትርፍ ማሽቆልቆል የገጠመው ኩባንያው “አሳፋሪ የማንቂያ ደውል” ደርሶታል ብለዋል።
ሜታ ምንም እንኳን በአውሮፓውያኑ 2022 ከ 23 በሊዮን ዶላር በላይ ማትረፍ ቢችልም የባለፈው ዓመት እስከ ታህሳስ ወር ባሉት ሶስት ወራት ትርፉ በ4 በመቶ ቀንሷል።
ዙከርበርግ በአሜሪካ ያታየው ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ፣ የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ሁኔታ አለመረጋጋት እና የቁጥጥር መጠናከር ሜታ ላይ ተጽእኖ እንዳደረገ እና ለትርፉም መቀነስ ምክንያት ነው እንደሆነ ጠቁመዋል።
“አዲሱ የምጣኔ ሃብት መንገራገጭ ለበርካታ ዓመታት ሊቀጥል ይችላል ብለን ራሳችንን ማዘጋጀት አለበን ብዬ አስባለሁ” ሲሉም አክለዋል።
የፌስቡክ የሠራተኞች ቅነሳ የተሰማው ጉግልና አማዞንን ጨምሮ ግዙፍ ኩባንያዎች የሠራተኛ ቅነሳን እና ተወዳዳሪነት ለማጣጣም እየታገሉ ባሉበት ወቅት ነው።
በፈረንጁ አዲስ ዓመት መግቢያ ላይ አማዞን ከ18 ሺህ በላይ ሠራተኞችን “በማያስተማመምነው ኢኮኖሚ” ምክንያት እንደሚቀንስ ያስታወቀ ሲሆን የጉግል ባለቤት አልፋቤት ደግሞ 12 ሺህ ሠራተኞችን ቀንሷል።
የሠራተኞችን ቅነሳ የሚከታተል አንድ ድረ-ገጽ እንዳወጣው መረጃ ከሆነ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከገባ በኃላ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች 128 ሺህ ሠራተኞችን ቀንሰዋል።