በአሜሪካ ከእስር ያመለጠውን የዕድሜ ልክ ፍርደኛ ለመያዝ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

ታትሟል

በአሜሪካዋ ፔንሲልቬኒያ ግዛት ከእስር ቤት ያመለጠን የዕድሜ ልክ እስረኛ ለመያዝ በሁለት ወረዳዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደረገ።

ከአንድ ሳምንት በፊት ከእስር ቤት ያመለጠው የ34 ዓመቱ ዳኔሎ ካቫልካንቴ ሰኞ ምሽት ሁለት ግዜ በደኅንነት ካሜራ ስለመታየቱ ጥቆማ ደርሶኛል ብሏል ፖሊስ።

ብራዚላዊው ግለሰብ ባለፈው ወር የቀድሞ ፍቅረኛውን በስለት ወግቶ በመግደሉ ነበር የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት።

የአሜሪካ ፖሊስ ወንጀለኛውን ለመያዝ የሚያስችል ጥቆማ ለሰጠ 10ሺህ ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ብሏል።

ካቫልካንቴ ባለፈው ሳምንት ነሐሴ 25 ታስሮ ከነበረበት እስር ቤት ጣሪያ ላይ ወጥቶ ማምለጡን የሲቢኤስ ምንጮች ተናግረዋል።

ወንጀለኛው ከእስር ማምለጡ እንደተሰማ ፖሊስ ታስሮ ከነበረበት ዌስትቸስተር እስር ቤት ዙሪያ የሚገኝ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ፍለጋ አካሂዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ማክሰኞ ምሽት ወንጀለኛው በደኅንነት ካሜራ በሌላ አካባቢ ሁለት ግዜ ከታየ በኋላ ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ የሚፈለግበት አካባቢ እንዲሰፋ ተደርጓል።

በደኅንነት ካሜራዎቹ የተቀረጹት ምስሎች ግለሰቡ በተክሎች ውስጥ በጀርባው ቦርሳ አንግቦ ሲጓዝ አሳይተዋል።

የፖሊስ አባል የሆኑት ሮበርት ክላርክ ወንጀለኛው “በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚገኝ አደገኛ” ግለሰብ ነው ብሎ የገለጹት ሲሆን ብራዚላዊው ምናልባት አሁን ላይ በድካም ሰውነቱ ዝሎ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ፖሊስ ግለሰቡ ቀን ላይ ጥንቅጥቅ ደን ውስጥ እየተደበቀ ምሽት ላይ ደግሞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ግምታቸውን ይሰጣሉ።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ ካቫለካንቴ ቤቱን ሰብሮ ከገባ በኋላ ከፍሪጅ ውስጥ ምግብ ሰርቆ መውጣቱን ለፖሊስ ተናግረዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት ነዋሪዎች በር እና መስኮቶቻቸው ዘግተው ንቁ ሆነው እንዲጠባበቁ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ፖሊስ ግለሰቡን ለመያዝ አነፍናፊ ውሾች፣ አሰሳ የሚያደርጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዲሁም በሰውነት ሙቀት የሰው እንቅስቃሴን የሚያሳይ ቴክኖሎጂን እየተጠቀሙ ነው።

ብራዚላዊው የዕድሜ ልክ እስር የተፈረደበት ከአንድ ዓመት በፊት የቀድሞ ፍቅረኛው ዲቦራ ብራንዳኦን ሁለት ልጆቿ ፊት በስለት ወግቶ መግደሉ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

ግለሰቡ እአአ 2017 ላይ በሌላ ሰው ግድያ በብራዚል ጭምር ይፈለጋል።

መርማሪዎች ግለሰቡ የቀድሞ ፍቅረኛውን የገደለው ፍቅረኛው በብራዚል ፖሊስ እንደሚፈለግ ካወቀች በኋላ ለፖሊስ ጥቆማ ለመስጠት ስትሞክር እንደሆነ ያምናሉ።