ሩሲያ በዩክሬን ያቀደችውን ‘የይስሙላ’ ምርጫ ምዕራባዊያን አወገዙ

የዩክሬን ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሩሲያ በቁጥጥሯ ሥር በሚገኙ የዩክሬን ግዛቶች ለማካሄድ ያሰበችውን ሕዝበ ውሳኔ ምዕራባዊያን አወገዙ።

ሕዝበ ውሳኔው በሩሲያ በሚደገፉ አራት የዩክሬን ግዛቶች ይካሄዳል። የሚቀርበው ምርጫም ከሩሲያ ጋር ስለመቀላቀል ይሆናል ተብሏል።

አሜሪካ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ “የይስሙላ” ያሉትን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) በበኩሉ ዕቅዱ ጦርነቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

በዕቅዱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔው ከመጪው አርብ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሉሃንስክ፣ ዶኔስክ ዛፖሪዚሃ እና ኬርሶን ክልሎች ይከናወናል።

አራቱ ክልሎች የዩክሬንን 15 በመቶ ግዛት ይሸፍናሉ። እንደ ሬውተርስ የዜና ወኪል ደግሞ ግዛቶቹ ሃንጋሪን ያክላሉ።

በጦርነት ውስጥ ግልጽ እና ገለልተኛ ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል የሚለው ጉዳይ በምዕራባዊያን ጥያቄ አስነስቷል።

የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ “ይስሙላ” ያሉትን የሩሲያ ዕቅድ አጣጥለዋል።

የዴሞክራሲ “ስቅላቅ” ያሉት ደግሞ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ናቸው።

“የዶንባስ ሕዝበ ውሳኔ በጣም አሳዛኝ ካልሆነ አስቂኝ ነው” ሲሉ ማክሮን በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ከሚካፈሉበት ኒው ዮርክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ገለልተኛ አገራት አቋማቸውን እንዲያስተካክሉም ጠይቀዋል። ዝምታ “ታሪካዊ ስህተት” ነው ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሌቫን በበኩላቸው አሜሪካ ምርጫውን እንደማትቀበለው ገልጸዋል። ምርጫውንም “የሉዓላዊት እና የአገር አንድነት መርሆዎችን የጣሰ” ሲሉ ገልጸውታል።

በወራሪ ኃይል የሚታቀድ ሕዝበ ውሳኔ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሰ ሲሆን ሕጋዊ ተቀባይነትም የለውም ያለው ደግሞ በአውሮፓ የደኅንነት እና ትብብር ድርጅት ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ አጋሮቻቸው ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ዜለንስኪ ረቡዕ ዕለት ለተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ በቪዲዮ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ብዙም ባልተለመደ መልኩ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ከምርጫው እና ጦርነቱ ጋር በተያያዘ ማክሰኞ አመሻሽ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

ይህ ባለመሆኑ ትኩረቱ ወደ ዛሬው ውሎ ተቀይሯል።

በጥቂት ቀናት ውስጥ ድምጽ ለመስጠት መታቀዱ ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት ለመውሰድ የምታደርገውን ሥራ ለማፋጠን እንደ ግፊት ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህ የሆነው ዩክሬን በዚህ ወር 8,000 ስኩዌር ኪሎሜትር ከሩሲያ ወታደሮች ማስለቀቋን ከገለጸች በኋላ ነው።

ግዛቶቹን ለራሷ ማካለሏ ሩሲያ ግዛቶቼ በምዕራባዊያን መሣሪያዎች እየተጠቁ ነው በማለት ጦርነቱን ለማስቀጠል ያላትን ፍላጎት የሚያሳካ ነው ተብሏል።

ምክንያቱም በርካታ ምዕራባዊያን ለዩክሬን የጦር መሣሪያ በመስጠት ራሷን እንድትከላከል እያገዙ በመሆኑ ነው።

ይህም ደም አፋሳሹን ጦርነት ይበልጥ ያባብሰዋል የሚል ስጋት አስከትሏል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ኃላፊ ጦርነቱ ሊራዘም ይችላል የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዩክሬን ውስጥ የጅምላ መቃብሮች በቅርቡ መገኘታቸው የሰላም ውይይቱን ያደናቅፈዋል ሲሉ ኃላፊው ፒተር ማውረር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአራቱ ክልሎች የሚገኙ የሩሲያ ደጋፊ መሪዎች ሕዝበ ውሳኔውን ደግፈዋል።

የሩሲያ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑት የሉሃንስክ አስተዳዳሪው ሊዮኒድ ፓስችኒክ “የጋራ ዓላማችን እና ሕልማችን ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

የሩሲያ የደኅንነት ካውንስል ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ሕዝበ ውሳኔውን “ታሪካዊ ፍትሕን” የሚያረጋግጥ እና የማይቀለበስ ብለውታል።

በሩሲያ የሚደገፉ አስተዳዳሪዎች እአአ ከ2014 ጀምሮ በዶኔስክ እና ሉሃንስክ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

ሁለቱም ክልሎች በአወዛጋቢ ሁኔታ በፕሬዝዳንት ፑቲን ነጻ ክልል መሆናቸው ከተገለጸ ከሦስት ቀናት በኋላ ነበር የዩክሬን ጦርነት የተጀመረው።

ሩሲያ ሉሃንስክን መቆጣጠር ችላ የነበረ ቢሆንም ዩክሬን የተወሰኑ በታዎችን ለማስለቀቅ ችላለች።

ብዙዎች የሩሲያን የሕዝበ ውሳኔ ጉዳይ እአአ በ2014 ክሬሚያን ወደ ግዛቷ ካቀላቀለችበት ሁኔታ ጋር እያመሳሰሉት ነው።