ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስራኤል የተካሄደውን ምርጫ የቤንያሚን ኔታኒያሁ ጥምር ፓርቲ አሸነፈ
በእስራኤል የተካሄደውን ምርጫ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጥምር ፓርቲ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆኗል።
ይህንንም ተከትሎ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በምርጫው ተቀናቃኛቸው የነበሩት ያሪ ላፒድ፣ ኔታኒያሁን እንኳን ደስ አልዎት ብለዋል።
ላፒድ ለተፎካካሪያቸው ደውለው መልካም እድልን የተመኙላቸው ሲሆን፣ ሥርዓቱን የተከተለ የሥልጣን ሽግግር እንደሚኖር አረጋግጠውላቸዋል።
ሊኩድ የተባለው የኔታኒያሁ ፓርቲ እና የቀኝ አክራሪው ሃይማኖታዊ ፓርቲ አጋሩ በጣምራ ከእስራኤል 120 የፓርላማ መቀመጫ 64ቱን እንዳሸነፈ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ የሆነው የመጨረሻ ውጤት አሳይቷል።
ውጤቱም ባልጠበቀ ሁኔታ የቀድሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣን የመለሰ ሆኗል።
ውጤቱም እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ኔታኒያሁ ላይ የተከፈቱት እና እሳቸው ግን የማይቀባሏቸውን የሙስና፣ ማጨበርበር እና እምነትን ማጉደል ክሶች እንዲያበቁ ያደርጋል።
ከዋናው ውጤት በፊት የነበሩ ቅድመ ውጤቶች ኔያኒያሁ እየመሩ እንደሆነ ካመላከቱ በኋላ፣ ባደረጉት ንግግር ለፓርቲያቸው ደጋፊዎች ባደረጉት ንግግር ያለምንም ልዩነት ሁሉንም እስራኤላዊ የሚያገለግል መንግሥት አቋቁማለሁ ብለዋል።
“ደኅንነታችንን መልሰን እናረጋግጣለን፣ የኑሮ ውድነትን እንቀንሳለን፣ ሰላማችንን ይበልጥ እናጠናክራለን እስኤልን በአገራት መካከል ኃያል የሚያደርጋትን ጥረት እንመልሳለን” ብለዋል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን በዘገቡት የመጨረሻ ውጤት መሠረት የኔታኒያሁ ሊኩድ ፓርቲ 32 መቀመጫ፣ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላፒድ ፓርቲ ደግሞ 24 መቀመጫ ያገኙ ሲሆን የቀኝ አክራሪው ብሔርተኛ ጽዮናዊ ፓርቲ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ የአንድነት ፓርቲ ደግሞ 12 መቀመጫ አግኝቷል።
የተቀረሩትን መቀመጫዎች ደግሞ የተለያዩ ፓርቲዎች ይዘዋቸዋል።
ኔታኒያሁ በንግግራቸው ጥምረታቸው የሚያካትቷቸውን ፓርቲዎች ባይጠቅሱም የጽዮናዊ ፓርቲን እንደሚያካትት ይጠበቃል።