የክሪሚያ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ክፉኛ መጎዳቱን የሳተላይት ምስሎች አመለከቱ

ታትሟል

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ የክሪሚያ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ መጠነ ሰፊ ጉዳት እንደደረሰበትና የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖችም እንደወደሙ የሳተላይት ምስሎች አሳዩ።

በሩሲያ በምትተዳደረው ክሪሚያ ምዕራብ አካባቢ የሚገኘው ሳኪይ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ማክሰኞ ዕለት ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመበት ሲሆን አንድ ግለሰብም ተገድሏል።

ለጥቃቱ ዩክሬን ኃላፊነቱን አልወሰደችም። አዲስ የወጡት የሳተላይት መረጃዎች ግን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።

ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው የፕላኔት ላብራቶሪ የወጡት የሳተላይት ምስሎች ፍንዳታውን ተከትሎ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ የተረፈውን መሬት ያሳያሉ።

የጦር አውሮፕላን ማረፊያው ዋናው መንደርደሪያ ያልተጎዳ ቢመስልም የሳተላይት ምስሎቹ ቢያንስ ስምንት አውሮፕላኖች መውደማቸውን ያሳዩ ሲሆንና በርካታ ጉድጓዶችም በግልጽ ታይተዋል።

አብዛኞቹ የጦር አውሮፕላኖችም ከሕንጻ ውጭ በአየር ማረፊያው በተወሰነ አካባቢ አርፈው የነበሩ ናቸው።  

የሳተላይት ምስሎች ከጉዳቱ በፊት እና በኋላ

ዩክሬንን በተመለከተ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሳተላይት ምስሎችን የሚከታተለው የፕላኔት ላብራቶሪ አየር ማረፊያው ከመጎዳቱ በፊትና በኋላ ያወጣቸው ምስሎች አውሮፕላን ማረፊያው ተጎድቶ ሊሆን እንደሚችል ያመለከቱ የመጀመሪያዎቹ ገለልተኛ ማረጋገጫዎች ናቸው።

ከዚህ ቀደም የፍንዳታውን መጠንና የደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ዝርዝር መረጃዎች እምብዛም አልነበሩም።

ነገር ግን አውሮፕላን ማረፊያው እንዴት እና በምን እንደወደመ አሁንም ግልጽ አይደለም።

ሩሲያ ፍንዳታው በመጋዘን ውስጥ የተቀመጠ ጥይት በመፈንዳቱ ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ትገልጻለች።

ዩክሬንም ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት አልወሰደችም። የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ለዚህ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉት “ግድየለሾቹ” የሩሲያ ወታደሮች ናቸው ብለዋል።

ሚኒስትር ኦለክሲይ ረዝኒኮቭ “ እኔ እንደማስበው በጦር አውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ያሉ የሩሲያ ጦር ወታደሮች በቀላሉ የሚታወቀውን “ በአደገኛ ቦታዎች ማጨስ ክልል ነው” የሚለውን ሕግ የጣሱ ይመስለኛል። ይኸው ነው!” ብለዋል።

የዩክሬን አየር ኃይልም በርካታ የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች መውደማቸውን ገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ በበኩላቸው ሁለት የተለያዩ አደጋዎች መኖራቸው ድንገተኛ አደጋን ሳይሆን ጥቃትን እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ዩክሬን ክሪሚያን ኢላማ የማድረግ መብትን በተመለከተም “ ዩክሬን አስፈላጊ ከሆነ ግዛቷን ለማስመለስ ብቻ ሳይሆን ወራሪዎቿን ለመግፋት አውዳሚ ኃይል መጠቀሟ ፍጹም ሕጋዊ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በክሪሚያ ውስጥ በዩክሬን የሚፈፀም ማንኛውም ጥቃት ጦርነቱን እንደማባባስ ይቆጠራል።

ባለፈው ወር የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዚደንት ዲሚትሪ ሜዲቬዴቭ፣ ዩክሬን ክሪሚያን ኢላማ ካደረገች “ ዋጋዋን የምታገኝበት ቀን ይጠብቃታል።” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

ክሪሚያ የዩክሬን አካል እንደሆነች ዓለም አቀፍ እውቅና ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ በጥቁር ባሕር የተከበበችው ክሪሚያ እንደ አውሮፓውያኑ 2014 በሩሲያ ተጠቃላለች። አብዛኞቹ ዩክሬናውያንም ይህ ለጦርነቱ ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ።

ማክሰኞ ዕለት የተከሰተውን ፍንዳታም ተከትሎ ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ባደረጉት ንግግር፣ ዩክሬን ጦርነቱ ከመጠናቀቁ በፊት ባሕር ገብ መሬቷን [ክሪሚያን] መልሳ መያዝ እንዳለባት እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ 2014 ክሪሚያን የራሷ አካል ያደረገችው በአብዛኛው የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች አብላጫ ድምጽ ባለው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት ነበር።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ሕዝበ ውሳኔውን ሕገ ወጥ ብሎታል።

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱም ምልክት የሌላቸው የሩሲያ ወታደሮች በርካታ ወሳኝ ቦታዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ በችኮላ የተካሄደ ነበር ተብሏል።

ሩሲያ ክሪሚያን ወደ ግዛቷ የመቀላቀል ሃሳብ የመጣው በሩሲያ የሚደገፈው የዩክሬን ፕሬዚደንት ለወራት የዘለቀውን የአውሮፓ ተቃውሞን ተከትሎ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ነው።

ክሪሚያ የሩሲያ አካል ከሆነች ከስምንት ዓመታት በኋላም በአውሮፓውያኑ የካቲት 24 ላይ፣ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ዘልቀው እንዲገቡ ክሪሚያን እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከፍታለች።

ጦርነቱ በበርካታ የዓለም አገራት ላይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተፅእኖ እያደረሰ ይገኛል።