ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ጦርነት ክራይሚያ ነጻ ወጥታ መጠናቀቅ አለበት ሲሉ ዜለንስኪ ተናገሩ
የዩክሬን ጦርነት በክራይሚያ የተጀመረ በመሆኑ ጦርነቱ ሲጠናቀቅም ክራይሚያን ነፃን በማውጣት መሆን አለበት ሲሉ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት የሩሲያ አየር ኃይል መሰረት በሆነ ቦታ ላይ ፍንዳታዎች ከተከሰቱ እና የአንድ ሰው ሕይወት ካለፈ ከሰዓታት በኋላ ነበር።
ዜለንስኪ በንግግራቸው ስለ ፍንዳታዎቹ ምንም ባይሉም የምሽት መግለጫቸውን ክራይሚያ ላይ ያተኮረ ነበር።
“ክሪሚያ የዩክሬን ስለሆነ እኛም በፍጹም አሳልፈን አንሰጥም’’ ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ሩሲያ ፍንዳታውን አቅልላ የተመለከተች ሲሆን አንድ ከፍተኛ የዩክሬን አማካሪ ዩክሬን ለፍንዳታው ኃላፊነቱን እንደማትወስድ ተናግረዋል።
ክሬይሚያ የዩክሬን አካል የነበረች ሲሆን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሕገ-ወጥ ባለው ሕዝበ ውሳኔ ከ2014 ጀምሮ ሩሲያ አካል ነች በማለት ጠቅልላ ይዛለች።
ብዙ ዩክሬናውያን ይህንን የክራይሚያን ጉዳይ ሩሲያ ከአገራቸው ጋር ለጀመረችው ጦርነት የመጀመሪያ እርምጃ አድርገው ይመለከቱታል።
ትላንት ማክሰኞ ከክራሚያ በስተ ምዕራብ በሚገኘው በኖቮፌዶሪቭካ አቅራቢያ በሚገኘው ሳኪ በተሰኘው የሩሲያ የጦር ሰፈር በሩሲያ ቱሪስቶች ተወዳጅ በሆኑ የባህር ዳርቻዎች አቅራቢያ በርካታ ፍንዳታዎች ተከስተዋል።
በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተዘዋወሩ ምስሎች በባሕር ዳርቻው ላይ የሚዝናኑ ሰዎች ፍንዳታዎቹን ተከትሎ ሲሯሯጡ አሳይተዋል። የዓይን እማኞች ቢያንስ 12 ፍንዳታዎችን እንደሰሙ ተናግረዋል።
በክራይሚያ የሚገኝ የሩሲያ የጤና ባለስጣን አንድ ሲቪል ሰው ሲገደል ሌሎች ስምንት ሰዎች ቆስለዋል ብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ፍንዳታዎቹ በአንድ የጦር መሳሪያዎች ማቆያ ውስጥ የተቀመጡ ጥይቶች ፈንድተው የተከሰተ ነው ሲል ቢናገርም እስካሁን ድረስ የተረጋገጠ ነገር የለም።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ረዳት የሆኑት ማይካሂሎ ፖዶሊያክ ዩክሬን ከፍንዳታው ጀርባ የለችም ሲሉ ያጣጣሉ ሲሆን ለዶዝድ ኦንላይን የቴሌቪዥን ጣቢያ "በፍጹም፣ እኛ ከዚህ ጋር ምን አገናኘን?’’ ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሬዘዳንት ዜለንስኪም ማክሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር ፍንዳታውን በቀጥታ ባይጠቅሱም ስለ ክራይሚያ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል።
“የሩሲያ ጦርነት በዩክሬን ላይ የተጀመረው ክራይሚያን በመውረር መሆኑን አንዘነጋም። ይህ የሩሲያ ጦርነት... ክሪሚያ ጋር ተጀምሮ በክራይሚያን ነፃ በማውጣት ማብቃት አለበት" ብለዋል።