ለወራት ሕዋ ላይ የቆዩ የቻይና ጠፈርተኞች ወደ ምድር ተመለሱ

ቻይና ቐሚ የጠፈር ጣቢያ በመገንባት ከአለማቀፉ የጠፈር ጣቢያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ አገር ነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሦስት ጠፈርተኞች በሕዋ ላይ በሚገኘው የቻይና የጠፈር ማዕከል ውስጥ ስድስት ወራትን ካሳለፉ በኋላ ወደ መሬት ተመለሱ።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ውስጥ ቲአንጎንግ የተሰኘው እና በግንባታ ላይ የነበረውን የቻይናን የጠፈር ጣቢያን ለመከታተል ነበር ባለሞያዎቹ ወደ ዚያው ያመሩት።

ግንባታው ከሳምንታት በፊት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው ጠፈርተኞቹ ለተተኪዎቻቸው በማስረከብ ነው ወደ ምድር የተመለሱት።

የቻይና ራስ ገዝ አስተዳደር ወደ ሆነቸው ኢነር ሞንጎሊያ ባለፈው እሁድ ነበር የቻይና የጠፈር ኤጀንሲ “ሙሉ በሙሉ የተሳካ” ያለውን ቆይታ አጠናቀው የተመለሱት።  

የቻይና የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ የጠፈርተኞቹ ቡድን መሪ እንዲሁም አባላት ወደ ምድር ከተመለሱ በኋላ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩበትን የድምጽ መልዕክት አሰራጭቷል።

ከጠፈር ጣቢያው ከተነሱ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ነበር በመሬት ላይ ባለው ጣቢያ ባልደረቦች ተረድተው ከመንኮራኩሯ የወረዱት።

የሚመለሱትን ጠፈርተኞች ለመተካት ሦሰት አዲስ ባለሞያዎች ረቡዕ ወደ ጠፈር ማዕከሉ ያመሩ ሲሆን፣ በዚህም የመጀመሪያውን በሕዋ ላይ የተደረገ ርክክብ አድርገዋል። አዲሶቹ ጠፈርተኞች ለስድስት ወራት ቆይተው ወደ ምድር ይመለሳሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ይህ የቻይና የጠፈር ጣቢያ በናሳ ከሚመራው እና ቻይና ከ11 ዓመታት በፊት ከተገለለችበት ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ቀጥሎ ሁለተኛው ቋሚ የጠፈር ጣቢያ በመሆኑ ከሌሎች ጣቢያዎች ልዩ ያደርገዋል።  

ይህ ጉዞም ቋሚ ጣቢያውን ለማቋቋም መደረግ ከነበረባቸው 11 ጉዞዎች መካከል ሲሆን፣ ጣቢያው ቢያንስ ለመጪዎቹ አስር ዓመታት ምንም አይነት የመሬት ስበት በሌለበት ሙከራዎችን ለማካሄድ የሚያስችል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲስ የተላኩት ባለሞያዎችም ለጣቢያው የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ይተክላሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ የቻይና የጠፈር ኤጀንሲ አስታውቋል።

ቻይና ከሶቪየት ኅብረት ብሎም ከአሜሪካ ቀጥሎ ጠፈርተኞቿን ወደ ሕዋ በመላክ ብሎም ቋሚ የጠፈር ጣቢያን በመገንባት ሦስተኛዋ አገር ናት።

የጠፈር ጣቢያው በሚኖረው የ10 ዓመት እድሜም ቻይና በየዓመቱ አዳዲስ ጠፈርተኞችን ትልካለች ተብሎ ይጠበቃል።

ቻይና እስከዛሬ የጠፈርተኞችን ምልመላ አካሂዳ ከማታውቅባቸው እንደ ሆንግ ኮንግ ካሉ የራስ ገዝ አስተዳደሮች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለቀጣይ የጠፈር ጉዞ እንዲያመለክቱ በሩን ከፍታለች።

እኤአ በ1970 የመጀመሪያውን ሳተላይት ያመጠቀችው ቻይና፣ ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ ከ200 በላይ ሮኬቶችን አምጥቃለች።