ብራዚላዊው ኮከብ ፔሌ የካንሰር ህመሙ ተባብሷል- ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ82 ዓመቱ ብራዚላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ፔሌ የካንሰር ህመሙ መባባሱን በህክምና ላይ የሚገኝበት ሆስፒታል ገለጸ።
የሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ሆስፒታል ከተኛ ከሦስት ሳምንታት በላይ ሆኖታል።
ገናን በሆስፒታል እንደሚያሳልፍ ሴት ልጁ በማህበራዊ ሚዲያ አስታውቃለች።
እስራኤላታ አልበርት አንስታይን የተባለው ሆስፒታል የፔሌ "የካንሰር ህመም እየተባባሰ ሲሆን ከኩላሊት እና የልብ ህመም ጋር የተያያዘ ከፍተኛ እንክብካቤ ያስፈልገዋል" ብሏል።
ፔሌ እአአ መስከረም 2021 ከአንጀቱ ውስጥ ዕጢ የተወገደለት ሲሆን ከዚያ በኋላ በመደበኛ የሕክምና ክትትል ያደርጋል።
የፔሌ ልጅ ኬሊ ናሲሜንቶ በኢንስታግራም ገጿ ላይ "ገና በቤታችን አይከበርም" ስትል ጽፋለች።
"በተለያዩ ምክንያቶች በአንስታይን ሆስፒታል የሚሰጠውን እንክብካቤ እያገኘ እዚህ ብንቆይ ይሻለናል በማለት ከሐኪሞቹ ጋር ወስነናል" ብላለች።
ፔሌ ሆስፒታል ከገባ በኋላ በሳኦ ፓውሎ የሚገኘው የህክምና ማዕከል "ለአተነፋፈስ ኢንፌክሽን ሕክምናው ጥሩ ምላሽ እየሰጠ ነው" በማለት ተናግሯል። "የኬሞቴራፒ ሕክምናው እንደገና እየታየ" መሆኑም ተገልጾ ነበር።
ፔሌ 92 ጊዜ ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ 77 ጎሎችን በማስቆጠር የሃገሩ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው። ብራዚልም በአውሮፓውያኑ 1958፣ 1962 እና 1970 የዓለም ዋንጫን እንድታነሳ አስችሏታል።
የብራዚል ተጫዋቾች በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ደቡብ ኮሪያን በሩብ ፍጻሜው ካሸነፉ በኋላ ስሙና ምስሉ ያለበትን ባነር በማውለብለብ ለፔሌ ክብር ሰጥተዋል።












