ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራናዊው የዶናልድ ትራምፕ አማካሪን ለመግደል በማሴር ተከሰሰ
ኢራናዊው የዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተንን ለመግደል በማሴር በአሜሪካ ክስ ቀረበበት።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ (አይአርጂ) አባል የሆነው ሻህራም ፑርሳፊ በአሁኑ ወቅት ኢራን ውስጥ እንደሚገኝ እና በተጠረጠረው የግድያ ሴራ እንደሚፈለግ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ግለሰቡ ግድያውን ያሴረው በአሜሪካ ጥቃት ለተገደሉት የኢራን ኃያል ወታደራዊ አዛዥ ቃሴም ሶለይማኒ የበቀል ምላሽ ሳይሆን እንዳልቀረም ተናግረዋል።
ሶለይማኒ በመካከለኛው ምስራቅ የነበረውን የኢራን ወታደራዊ ዘመቻን መርተዋል።
የ62 አመቱ ወታደራዊ አዛዥ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃን ቡድን ኃይል የመሩ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2020 በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ በኢራቅ፣ በባግዳድ አየር ማረፊያ መገደላቸው ይታወሳል።
የግለሰቡን ክስ አስመልክቶ የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ “ክሱ መሰረተ ቢስ ነው” ሲሉ ለመንግሥት ሚዲያ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የፍትሕ ዲፓርትመንት ክሱን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳሳወቀው መህዲ ሬዛይ በመባል የሚታወቀው የ45 አመቱ ፑርሳፊ በዋሽንግተን ዲሲ ወይም ሜሪላንድ ግድያው እንዲፈጸም አሜሪካ ላሉ ግለሰቦች 300 ሺህ ዶላር ከቴህራን ሆኖ ለመክፈል ሞክሯል።
በተጨማሪም በክሱ ላይ ፑርሳፊ በኢንተርኔት ላይ ላገኘው አንድ አሜሪካዊ የቀድሞ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተንን ፎቶ እንዲያነሳው የጠየቀ መሆኑም ቀርቧል። ለዚህም እንደ ሽፋንነት የተጠቀመው "መጽሐፍ እየጻፍኩ ነው" የሚል እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ ስሙ ያልተጠቀሰ አሜሪካዊ ፑርሳፊን ሌላ ግለሰብ ጋር እንዳስተዋወቀው ያተተው ክሱ፣ ይህ ግለሰብ ጆን ቦልተንን እንዲገድል ለግድያው ማስረጃም ቪዲዮ እንዲልክ ተጠይቋል ብሏል።
ጆን ቦልተን ኤፍ ቢ አይን እና የፍትሕ ክፍሉን ለዚህ ተግባራቸው አመስግነው መግለጫ አውጥተዋል።
"የፍትሕ ክፍሉ ዜጎቻችንን ሊጎዱ ወይም ሊገድሏቸው ከሚፈልጉ ከጠላት መንግሥታት የመጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት አለበት" በማለት ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማቲው ጂ ኦልሰን መናገራቸው ተዘግቧል።