በኬንያ አንዲት መምህር ያለማቋረጥ ከሁለት ቀን በላይ አስተማረች

ሮዝ ታታ ዌኬንሳ የተባለችው መምህር ስታስተምር

የፎቶው ባለመብት, Rose Tata Wekesa/YouTube

ታትሟል

በኬንያ ሮዝ ታታ ዌኬንሳ የተባለች አንዲት መምህር ያለማቋረጥ ለረዥም ጊዜ የሳይንስ ትምህርት በመስጠት ክብረ ወሰን ለመሰበር የሚያስችላትን ቆይታ አድርጋለች። መምህርቷ ያለማቋረጥ ለ50 ሰዓታት ትምህርት ሰጥታለች።

መምህር ሮዝ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሚገኝ ትምህርት ተቋም ባለ ቤተ ሙከራ ውስጥ ከሁለት ቀናት በላይ ያለማቋረጥ ስታስተምር ቆይታ ልክ 50 ሰዓት ሲሟላት የመማሪያ ክፍሉ በደስታ ሁካታ ተሞልቷል።

ሆኖም የመምህርት ሮዛ ፍላጎት እዚህ ላይ አይገታም። ያለማቋረጥ ከዚህም በላይ ማስተማር ትፈልጋለች። በዚህም ምክንያት ትምህርቱ ይህ ዘገባ እከሚጠናከርበት ጊዜ ቀጥሏል።

ይህ ክብረ ወሰን እንደሆነ የተገመተው ቆይታ በዓለም ዙሪያ ድንቃ ድንቆችን በሚመዘግበው ጊነስ የዓለም ክብረ ወሰኖች መዝገብ ለመሰፈር ተቋሙ ማጣራት እያደረገ ነው።

ሮዝ ታታ ዌኬንሳ በኬንያ ናይሮቢ በሚገኘው ሴንት ኦስትቲንስ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ውስጥ የባዮሎጂ እና ኬሚስትሪ መምሀር ናት።

መምህርቷ ይህንን ስኬት ከማስመዝገቧ አንድ ወር ቀደም ብሎ በኬንያ ከሚገኘው እና ሲቲዝን ከተሰኘው የግል ሚዲያ ጋር ባደረገችው ቆይታ ይህንን ያህል ሰዓት ማስተማር ስለፈለገችበት ምክንያት አስረድታለች።

“የሳይንስን ሁለትዮሽ እና አስገራሚ ገጽታን ለማሳየት” ይህንን ማድረጓን ገልጻለች።

ቀጥላም፣ “ መምህራን ከክፍል ባሻገር ትልቅ ስኬትን ማስመዝገብ እንደሚችሉ በማሳየት፣ መምህር መሆን የሚፈልጉ ተማሪዎችን ማነሳሳት እፈልጋለሁ” ስትል ተናግራለች።

መምህርቷ የምትሰጠው ትምህርት በኢንተርኔት (ዩቲዩብ) አማካኝነት በቀጥታ እየተሰራጨ ይገኛል። በዚህ የቀጥታ ስርጭት ተማሪዎች ጥያቄ ሲጠይቁ እና ሲሳተፉም ይታያል።

መምህርቷ ባለፈው ጥቅምት ወር እስከ 60 ሰዓታት የማስተማር እቅድ እንዳላት ገልጻ ነበር። ያ ካልሆነ ግን ክብረ ወሰኑን ለመስበር ቢያንስ 50 ሰዓታት ማስተማር አቅዳ ነበር። በዕቅዷ መሰረት ረቡዕ የካቲት 6/2016 ዓ.ም የተጀመረው ትምህርት እሰከ ዛሬ አርብ የካቲት 8 መቀጠሉን የኬንያ ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

መገናኛ ብዙኃኑ እንደዘገቡት የናይሮቢ የቀድሞ ገዢ ማይክ ሶንኮ ኬንያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉላት ጠይቋል።

መምህርቷ ገላዋን ለመታጠብ፣ ምግብ ለመመገብ፣ የህክምና ዕይታ ለማግኘት እና ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ የ20 ደቂቃ እረፍት እንደምትወስድም ተዘግቧል።