ፕሪሚየር ሊጉ ማንችስተር ሲቲ ላይ ያቀረባቸው ክሶች እና የክለቡ ዕጣ ፈንታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ የፋይናንስ ሕጎቼን ጥሷል በሚል ክለቡ ላይ ክስ ለመመስረት መወሰኑ ይፋ መሆኑ የሊጉ መነጋገሪያ ሆኗል።
ክለቡ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በቅቷል። በአቡዳቢ ዩናይትድ ግሩፕ እአአ በ2008 ከተገዛ በኋኀዓ ስድስት ሊግ ዋንጫዎችን ከፍ አድርጓል።
ለመሆኑ ሲቲ እንዴት እዚህ ውጥንቅት ውስት ገባ? ክሶቹስ ምን ያህል አሳሳቢ ናቸው? ክፕሪሚየር ሊጉስ ሊባረሩ ይችላሉ?
ቢቢሲ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ይዟል።
ሲቲ ለምን ተከሰሰ?
ከአራት ዓመታት ምርመራ በኋላ ፕሪሚየር ሊጉ ማንችስተር ሲቲ ከ100 በላይ የፋይናንስ ሕጎችን ጥሷል በሚል ክስ መመስረቱን አስታውቋል።
“ክሱን ካየነው ሁለት ነገሮችን ይዟል” የሚለው እግር ኳስ ፋይናንስ ባለሙያው ኬራን ማጓየር ነው።
“የመጀመሪያው ማንችስተር ሲቲ ከስፖንሰርሺፕ እና ከማስታወቂያ ያገኘውን ገቢ ከመጠን በላይ አጋኖ ማቅረቡ ነው። ፕሪሚየር ሊጉ እንደሚለው ከሆነ ተጨማሪው ገንዘብ ወደ ክለቡ የገባው ከሲቲ ባለቤቶች ኪስ ነው። ይህ ደግሞ ፍትሐዊ የፋይናንስ አጠቃቀም (ፋይናንሺያል ፌይር ፕሌይ) ላይ አይካተትም” ይላል።
“ሌላኛው ክስ ደግሞ ማንችስተር ሲቲ ሥራ ማስኬጃ ወጪውን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል የሚል ነው። ለዚህ እንዲረዳቸው የሥራ ኃላፊዎች በባለሃብቶቹ በተያዙ ኩባንያዎች ውል እንዳላቸው በማስመሰል የክለቡን ትክክለኛ ወጪ ቀንሰው አቅርበዋል።"
ሲቲ እንዴት ከዚህ ደረሰ?
እአአ በ2018 ዴር ስፒገል የተባለ የጀርመን ጋዜጣ አንድ ሾልኮ የወጣ መረጃ አስነብቦ ነበር። ሲቲ የስፖንሰር ገቢውን ያለልክ በመጨመር የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን በማታለል ፍትሐዊ የፋይናንስ አጠቃቀምን ለመጣስ ተጠቅሞበታል ብሎ ነበር።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ሲቲ ከ2012 እስከ 2016 ድረስ ፍትሐዊ የፋይናንስ አጠቃቀምን ተላልፏል ሲል ወሰነ።
ማንችስተር ሲቲ ለሁለት ዓመታት ከአውሮፓ ውድድሮች እንዲታገድ የተላለፈው ውሳኔ ግን በስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።
የፕሪሚየር ሊጉ ምርመራ በ2018 ነው የተጀመረው። ሲቲ ውንጀላዎቹ “በሙሉ የውሸት” ናቸው ያለ ሲሆን የጋዜጣው ዘገባም “ከሕገ-ወጥ የመረጃ ብርበራ የተገኘ ነው” ብሏል።
ምን ያህል ተጽዕኖ ይኖረዋል?
የቢቢሲው የስፖርት አርታኢ ዳን ሮአን “ይህ ፕሪሚየር ሊጉ ትልቁ ቅሌት ነው። የትኛውም ክለብ በዚህ ደረጃ ክሶች ቀርበውበት አያውቁም” ይላል።
“ማጭበርበሩ ከተረጋገጠ በእንግሊዝ እግር ኳስ የበላይ በመሆን ላይ ላለው ክለብ፣ ለአቡ ዳቢ ባላሃብቶች፣ በመንግስት ባለቤትነት ለሚተዳደሩ ክለቦች እና ለፍትሃዊ ውድድር መርህ ጉዳት ነው።“
“ሕጉን አልጣስኩም በሚል ክለቡ ቃል የገባለት አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም ከዚህ ቀደም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ክለቡ ሕጉን ከጣሰ ኃላፊነቱን እንደሚለቅ ተናግሯል።”
“ይህ ለወራት የሚዘልቅ ሲሆን ፕሪሚየር ሊጉ ላይም ጥላውን ያሳርፋል” ብሏል።
ማንቸስተር ሲቲስ ምን አለ?
ሲቲ በክሱ “መገረሙን” አስታውቋል። ምክንያት ያለው ደግሞ “በርካታ ግንኙነቶችን ማድረጉን እና ዝርዝር መረጃዎች” ለፕሪሚየር ሊጉ በመስጠቱ ነው።
“ጉዳዩ በገለልተኛ ኮሚሽን መታየቱንም” ተቀብሏል።
“ጉዳዩንም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት ተዘጋጅተናል” ብሏል ክለቡ።
ሲቲ በጉዳዩ ዙሪያ ልበ ሙሉ መሆኑ ተነግሯል። በክሶቹ ዙሪያ ወቅቱን ጠብቆ መረጃዎችን ለሊጉ መስጠቱንም ክለቡ ያምናል።
ማንችስተር ሲቲ ምን ይጠብቀዋል?
ሲቲ የሕግ ጥሰቶቹን ከፈጸመ ቅጣት እና የነጥብ ቅነሳን ጨምሮ ከፕሪሚየር ሊጉ እስከመባረር የሚደርስ ውሳኔ ኮሚሽኑ ሊያስተላልፍ ይችላል።
“ውሳኔዎቹ ድንበር የለሽ ናቸው” ሲሉ ማጓየር ተናግረዋል።
“ድጋሚ እንዳታደርጉት ከሚል ማስጠንቀቂያ እስከ ቅጣት፣ የነጥብ ቅነሳ፣ ያሸነፉትን ዋንጫ መንጠቅ እና ከፕሪሚየር ሊጉ እስከ ማባበረር ሊደርስ ይችላል።”
እአአ በ2011 ኪውፒአር የዝውውር ሕጎችን በመጣሱ የነጥብ ቅነሳ ባይገጥመው 875 ሺህ ፓውንድ ተቀጥቷል። ሌስተር እና በርንማውዝ ወደ ሊጉ ሲያድጉ ፍትሐዊ የፋይናንስ አጠቃቀምን ተላለፈዋል በሚል ቅጣት ተላለፎባቸዋል።
ሬንጀርስ እአአ በ2012 የአስተዳደር ቀውስ በገጠመው ወቅት በስኮትላንድ እግር ኳስ ማህበር እና ፕሪሚየር ሊግ ያላቸው ምዝገባ ተሰርዞ በእግር ኳስ ሊጉ የታችኛው እርከን እንዲወዳደር ተገዷል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የጣሊያኑ ጁቬንቱስ በዝውውር ጥሰቶች ምክንያት 15 ነጥቦች ተቀንሰውበታል።
“ከእገዳ አንጻር የሚይዛቸው ነገር አይታየኝም” ይላል ኩኪር።
“ለኮሚሽኑ ጥያቄ የሚሆነው የትኛው ውሳኔ ተገቢ ነው ብሎ ማሰቡ ነው” ብሏል።












