ትላትል እየተመገበ 31 ቀናትን አማዞን ጫካ ውስጥ ያሳለፈው ግለሰብ

ጆናታን አኮስታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የ30 ዓመቱ ጆናታን አኮስታ ሰሜናዊ ቦሊቪያ ውስጥ ከአራት ጓደኞቹ ጋር አደን ላይ ሳለ ነው ተገንጥሎ የጠፋው።

ቦሊቪያዊው ግለሰብ ለ31 ቀናት ያክል ትላትል እየተመገበ ሕይወቱን እንዳቆየ ያወሳል።

ጫማውን እንደ አሸንዳ ተጠቅሞ የሰበሰበውን የዝናብ ውሃ እየጠጣ ትላትልና በራሪዎችን እየተመገበ ከአዳኝ አውሬዎች እየሸሸ ነው አንድ ወር ያህል የቆየው።

የአኮስታ ቤሰተቦችና ጓደኞቹ እንዲሁም የአካካቢው ማሕበረሰብ ለአንድ ወር ከፈለጉት በኋላ በስተመጨረሻ ሊያገኙት ችለዋል።

“በጣም የሚደንቅ ነው። ይህ ያህል ጊዜ ሰዎች እኔን ፍለጋ ይሰማራሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር” ብሏል አኮስታ።

“ትላትል በልቻለሁ፤ በራሪ ነገሮችን ተመግቤያለሁ። ሕይወቴን ለማትረፍ ያደረግኩትን ብነግራችሁ አታምኑም” ሲል ከሆስፒታል አልጋው ላይ ሆኖ ታሪኩን አጋርቷል።

በአካባቢው ማሕበረሰብ ጋርጋርቶስ በመባል የሚታወቅ ፓፓያ የመሰለ ፍሬ ሲመገብ እንደነበረም ተናግሯል።

“ፈጣሪዬ አዲስ ሕይወት ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ”።

ቤተሰቡ ለጊዜው የአኮስታ ስነ-ልቡናዊ ጤንነት እስኪያገግም እየተንከባከቡት እንደሆነ ገልጠው ጤናው መለስ ሲል እንዴት ሊጠፋ እንደቻለ እንደሚጠይቁት ተናግረዋል።

አኮስታ በአማዞን ቆይታው 17 ኪሎግራም ክብደት ቀንሶ፤ አልፎም ጉልበቱ ላይ ጉዳት ደርሶበትና የፈሳሽ እጥረት ገጥሞት ሳለ ነው በአካባቢው ማሕበረሰብ የተገኘው።

እንደዚያም ሆኖ እያነከሰ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀስ ነበር።

“ወንድሜ በአራተኛው ቀን ጉልበቱ ላይ ጉዳት ከገጠመው በኋላ ለሕይወቱ ይሰጋ እንደጀመር ነግሮናል” ሲል ወንድሙ ሃሮሺዮ አኮስት ለቦሊቪያው ፓጊና ሲዬት ጋዜጣ ተናግሯል።

“በያዘው የአደን መሣሪያ ውስጥ ውስጥ ጥቂት ቀለሃ ብቻ ነበረው። መራመድ አይችልም ነበር። ማንም እሱን ፍለጋ ይመጣል ብሎ አልገመተም ነበር።”

አኮስታ በጠፋ ጊዜ ገጀራም ሆነ ባትሪ አልያዘም ነበር። በጫማው የዝናብ ውሃ እያቋተ ነው ሲጠጣ የከረመው።

ጃጓር የተሰኘው ነብር መሰል የዱር እንስሳ ጋር ተፋጦ እንደነበርም ለቤተሰቦቹ ተናግሯል።

በደቡብ አሜሪካው ግዙፍ ጫካ ውስጥ የሚገኙ አውሬዎችን ለማባረር የቀረውን ቀለሃ እንደተጠቀመም ታናሽ ወንድሙ ገልጧል።

በ31ኛው ቀን 300 ሜትር ርቀት ላይ የሰዎች ድምፅ ሲሰማ እያነከሰና እየጮኸ ድምፅ ወደሰማበት አቅጣጫ በመሮጥ ሕይወቱን አድኗል።

አራት የሥፍራው ሰዎች ናቸው አኮስታ “አድኑኝ” እያለ ወደነሱ ሲመጣ የተመለከቱት።

“አንድ ሰው ወንድማችሁን አገኘነው እያለ ወደኛ እየገሰገሰ ሲመጣ አላመንነውም ነበር” ይላል ወንድሙ።

ሃሮሺዮ እንደሚለው ታላቅ ወንድሙ ከዚህ በኋላ አደን የሚባል ነገር እንደማያስብ ለቤተሰቡ ቃል ገብቷል።

“ፈጣሪውን ለማመስገን ሙዚቃ ይጫወታል። ለፈጣሪ የገባው ቃል ነው። ቃሉን እንደሚጠብቅ እምነት አለኝ” ሲል ጊታር የሚጫወተው ወንድሙ የወደፊት ዕቅዱን ተናግሯል።

በሌላ በኩል ፖሊስ አራቱን የአኮስታ ጓደኞች እንዴት ከነሱ ተገንጥሎ ሊጠፋ እንደቻለ እንደሚጠይቅ ገልጧል።