የጂ7 መሪዎች ሩሲያ በዩክሬን የገበያ ማዕከል የሰነዘረችው የሚሳኤል ጥቃት ከ‘ጦር ወንጀል’ አይተናነስም አሉ  

ታትሟል

ሩሲያ በዩክሬን ከተማ ክረመንቹክ በሰነዘረችው የሚሳኤል ጥቃት 16 ሰዎች ተገድለዋል።

በጀርመን የተሰበሰቡት ሰባቱ የብልጹግ አገራት መሪዎች ይህን ጥቃት በብርቱ ኮንነዋል።

ጥቃቱን ‘የጦር ወንጀል’ ሲሉም ጠርተውታል።

በዚህ የገበያ ማዕከል የሚሳኤል ጥቃቱ ሲሰነዘር አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በሥፍራው አገር ሰላም ብለው ሲገበያዩ እንደነበረ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለነስኪ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ሰባቱ ብልጹግ አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ንጹሐን ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸም በማያሻማ ሁኔታ የጦር ወንጀል ነው ብለዋል።

በጥቃቱ ከሞቱት በተጨማሪ 59 ሰዎች ቆስለዋል።

የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተፈርቷል።

የገበያ ሕንጻው አናት በእሳት ተያይዞ ሲነድ የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ሲዘዋወሩ ውለዋል።

ዘለንስኪ ይህ ጥቃት በአውሮፓ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል ብለዋል።

ዘለንስኪ እንዳሉት ይህ የገበያ ሥፍራ ለሩሲያ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው አይደለም።

“ሩሲያን ያበሳጫት ምናልባት በሰላም ሕይወታቸውን ለመምራት የቆረጡ ሰዎች በዚያ ሕንጻ መኖራቸው ይሆናል” ብለዋል ዘለንስኪ።

ጨምረውም፣ “ያበዱ አሸባሪዎች ካልሆኑ በስተቀር፣ ምድር ላይ ለሕይወት ቦታ የማይሰጡ አሸባሪዎች ካልሆኑ በስተቀር እንዲህ ዓይነት የሚሳኤል ጥቃት በንጹሐን ላይ ማን ይሰነዝራል?’ ሲሉ ተናግረዋል።

የአካባቢው ገዥ ዲሚትሮ ሉኒን በበኩላቸው ጥቃቱ ‘በመላው የሰው ዘር ላይ የተሰነዘረ’ ሲሉ ክብደቱን በመግለጽ አውግዘውታል።

በርካታ ሰዎች በገበያ ሕንጻው ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ቤተሰቦች በአቅራቢያው በሚገኝ ሆቴል ተሰብስበው ከአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሚመጣን ዜና በጭንቅ እየተጠባበቁ ታይተዋል።

ይህ የሚሳኤል ጥቃት በአገሬው አቆጣጠር ከሰዓት ወደ 10፡00 ሰዓት ገደማ ነበር የተፈጸመው።

ሕንጻው ሲነድ እየመሸ ስለነበረም ጄኔሬተሮች ወደ ሕንጻው ተጠግተው መብራት በመለኮስ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሌሊቱን በሙሉ በሕይወት ያሉ ሰዎችን ፍለጋ ለማሳለፍ ሲዘጋጁ ተስተውለዋል።

ማዕከላዊ ምሥራቅ ክሬመንቹክ ሩሲያ ከምትቆጣጠረው አካባቢ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የኢንዱስትሪ ከተማ ነው።

ወደ 220ሺህ ሰዎች በዚህ ከተማ ይኖራሉ።

ይህ ጥቃት ሲሰነዘር የብልጹግ አገር መሪዎች ማለትም አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ዩኬ፣ ጀርመን ጣሊያንና ካናዳ በሩሲያ ጉዳይ ላይ እየመከሩ ነበር።

ጥቃቱን ተከትሎ ታዲያ ብልጹግ አገራቱ ማንኛውንም ዓይነት የመሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ለዩክሬን እስከመጨረሻው ድረስ ለመለገስ ቃል ገብተዋል።

በሩሲያ ላይም ተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ማዕቀቦችን ጥለዋል።