በአሜሪካ አንድ የስድስት ዓመት ተማሪ መምህሩን በጥይት ክፉኛ አቆሰለ

ክስተቱ ያጋጠመው ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ ኒውፖርት ኒውስ ከተማ በሚገኘው ሪችኔክ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ክስተቱ ያጋጠመው ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ ኒውፖርት ኒውስ ከተማ በሚገኘው ሪችኔክ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው
ታትሟል

አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የስድስት ዓመት ታዳጊ ልጅ አንዲት መምህሩ ጋር ከተፈጠረ አለመግብባት ጋር በተያያዘ ጥይት ተኩሶ ጉዳት እንዳደረሰባት ፖሊስ አስታወቀ።

ጥቃቱ የተፈጸመው ኒውፖርት ኒውስ በተባለችው ከተማ ሪችኔክ በተባለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ መሆኑን የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ስቲቭ ድሪው ተናግረዋል።

ማንቱ ያልተገለጸው ታዳጊ ተማሪ በመምህሩ ላይ በሽጉጥ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በፖሊስ መያዙም ተገልጿል።

ታዳጊው እንዴት ሽጉጥ ሊያገኝ እንደቻለ ግልጽ ባይሆንም፣ የፖሊስ አዛዡ ተኩስ የተፈጸመው “በድንገት በተተኮሰ ጥይት” አለመሆኑን አመልክተዋል።  

በጥይት የተመታችው መምህርት ማንነት ያልተገለጸ ሲሆን፣ በ30ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ናት ተብሏል። በጥቃቱም ለሕይወት አስጊ ጉዳት ደርሶባታል።

መምህርቷ በጥይት ከተመታች በኋላ በአካባቢው ወደ ሚገኝ ሆስፒታል ተወስዳ በሐኪሞች የቅርብ ክትትል እየተደረገላት ነው።

ክስተቱ ያጋጠመው ከስድስት አስከ ሰባት ዓመት የሚሆኑ ተማሪዎች በሚገኙበት አንደኛ ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ በመምህርቷ እና በታዳጊው መካከል ጭቅጭቅ ከተፈጠረ በኋላ ነው ጥይት የተተኮሰው።

ፖሊስ ይህ ያጋጠመው ተኩስ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያጋጠመ አንድ የተናጠል ክስተት ብቻ እንጂ “የፖሊስን ጣልቃ ገብነት የፈለገ በርካታ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ በሌሎች ቦታዎች እንደተፈጸመ አይነት የትምህርት ቤት ጥቃት አይደለም” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት 550 ያህል ተማሪዎች ያሉት ትምህርት ቤት መግቢያው ላይ ዘመናዊ የመፈተሻ መሳሪያ ያለው ሲሆን፣ በሁሉም ላይ ሳይሆን በተመረጡ ተማሪዎች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ይደረግበት ነበር።

ፖሊስ ታዳጊው ተማሪ አስተማሪው ላይ የተኮሰበት የመሳሪያ ሽጉጥ ከመሆኑ ውጪ ምን አይነት እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የአካባቢው ትምህርት ቤቶች ኃላፊ ዶ/ር ጆርጅ ፓርከር እንዳሉት ባለሥልጣናት “ይህንን ክስተት ያስከተለውን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ” እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

“ይህ አስደንጋጭ ክሰተት ነው፤ ተመሳሳይ ነገር ፈጽሞ መከሰት የለበትም” ሲሉ ዶ/ር ፓርከር ከአክለዋል። “ይህ ሁኔታ በድጋሚ እንዳያጋጥመን እርግጠኛ መሆን እንፈልጋለን።”

ትምህርት ቤቱ ሰኞ ዕለት ዝግ እንደሚሆንና ከተከሰተው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው የተፈጠረባቸውን አሰቃቂ ሁኔታ እንዲቋቋሙ ለማድረግ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ኃላፊው ቃል ገብተዋል።

ከሦስት ቀናት በፊት ሥልጣናቸውን የተረከቡት የከተማዋ ከንቲባ ፊሊፕ ጆንስ፣ ክስተቱ ለከተማቸው ኒውፖርት ኒውስ “ጥቁር ቀን ሆኖ ይታሰባል” ብለዋል።

“ከዚህ ሁኔታ ተምረን ለወደፊቱ ጠንካራ ሆነን እንወጣለን” ሲሉ ከንቲባው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የቨርጂኒያ ግዛት ገዢ የሆኑት ግሌን ዩንኪን ክስተቱ ለተፈጠረበት ከተማ ባለሥልጣናት አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፣ አስተዳደራቸው “በሚችለው ሁሉ ድጋፉን ለመቀጠል ዝግጁ ነው” በማለት አክለዋል።

“ሁኔታውን መከታተሌን እቀጥላላሁ፣ እንዲሁም ለሁሉም ተማሪዎች እና ለማኅበረሰቡ ደኅንነት መጠበቅ ጸሎት አድርጋለሁ” ብለዋል ከንቲባው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት።

በቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የኒውፖርት ኒውስ ከተማ 180,000 የሚደርስ ነዋሪ ያላት ስትሆን፣ ከግዛቲቱ ዋና ከተማ ሪችመንድ በስተደቡብ 112 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።