ሰሜን ኮሪያ በፊኛ አማካይነት ቆሻሻ ደቡብ ኮሪያ ላይ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ ቆሻሻ እና የፕሮፓጋንዳ በራሪ ወረቀት የያዙ 90 ፊኛዎችን በደቡብ ኮሪያ ሁለት የድንበር ግዛቶች ላይ መጣሏ ተገለጸ።
የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣኖች ዜጎቻቸው ከቤት እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ነጫጮቹን ፊኛዎች ዜጎች እንዳይነኳቸውም የአገሪቱ መከላከያ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ነጫጮቹ ፊኛዎች ላይ የታሰሩት ፕላስቲኮች “አስቀያሚ ቆሻሻ” ስለያዙ የአገሪቱ ነዋሪዎች እንዳይነኳቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
ፊኛዎቹ የተገኙት ጊዮንጊ እና ጋንግዎን በተባሉ ግዛቶች ነው። በግዛቶቹ ምርመራ እየተደረገም ነው።
ከ1950ዎቹ ጦርነት በኋላ ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት ፊኛ ተጠቅመዋል።
ከዚህ ቀደም በደቡብ ኮሪያ የተጣሉ “በራሪ ወረቀትና ሌሎች ቆሻሻዎች” ለመበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ሰሜን ኮሪያ ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ ቆይታለች።
የሰሜን ኮሪያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ኪም ካንግ “ብዙ ቆሻሻ ደቡብ ኮሪያ ድንበር አካባቢ የሚጣል ይሆናል። ለማጽዳት ምን ያህል እንደሚወስድ ማወቅ አለባቸው” ብለዋል።
በሴዑል አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ከቤት ውጭ ከሚደረግ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
“ምንነቱ ያልታወቀ” ነገር ከተመለከቱ ጥቆማ እንዲሰጡም ተጠይቋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተዘዋወሩ ምሥሎች በፊኛ ላይ በታሰሩ ፌስታሎች ውስጥ የሽንት ቤት ወረቀት፣ አፈር፣ ባትሪ ድንጋይና ሌሎችም ቆሻሻዎች ታይተዋል።
ፖሊሶችና ወታደሮች በእነዚህ ፊኛዎች አቅራቢያ ምርመራ ሲያደርጉም ተስተውሏል።

የፎቶው ባለመብት, South Korean military
የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ዮንሀፕ “ከወደቁት ፊኛዎች መካከል አይነ ምድር ይገኝበታል” ሲል ዘግቧል።
ድርጊቱ ዓለም አቀፍ መርሕን እንደሚጻረር መከላከያው አስታውቋል።
“የዜጎቻችንን ደኅንነት አደጋ ውስጥ ይጥላል። በፊኛዎቹ ምክንያት ለሚፈጠረው ጉዳት ሰሜን ኮሪያ ተጠያቂ ናት። ይሄን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዲያቆሙ እናስጠነቅቃለን” ብሏል።
ከዚህ ቀደም የደቡብ ኮሪያ የመብት ተሟጋቾች ፒዮንግያንግን የሚቃወም ፕሮፓጋንዳ፣ ገንዘብ፣ ዕገዳ የተጣለበት የመገናኛ ብዙኃን ይዘትና በሰሜን ኮሪያ የታገደ ምግብ በፊኛ ልከው ነበር።
በፊኛዎቹ ውስጥ የኮርያ ሙዚቃ የያዘ ፍላሽ ዲስክና ቪድዮዎችም መላካቸውን የመብት ተሟጋቾች ገልጸዋል።
የሴዑል ምክር ቤት በ2020 ባወጣው መመሪያ ፒዮንግያንግን የሚጻረር ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ሕገ ወጥ ነው።
ሕጉ የመናገር ነጻነትና ሰብአዊ መብትን የሚገዳደር ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል።
ከዚህ በፊት ሰሜን ኮሪያ የደቡብ ኮሪያ መሪዎችን ለማጥቃትም ፊኛዎች ልካ ታውቃለች።
በ2016 የሽንት ቤት ወረቀት፣ የሲጋራ ቅሪትና ቆሻሻ በፊኛ ተልኮ ነበር። ፖሊስ “ለጤና አስጊ ባዩኬሚካል” ሲል ነበር የገለጸው።












