ኤሚሬትስ ገንዘቤን አላገኘሁም በሚል ወደ ናይጄሪያ የሚደርገውን በረራ ሊያቋርጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግዙፉ የዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ አየር መንገድ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ የማደርገውን በረራ ሊያቋርጥ መሆኑን አስታወቀ።
ዋና መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው ኤሚሬትስ አየር መንገድ የናይጄሪያ በረራውን ከነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚያቆም ገልጿል።
ኤሚሬትስ ወደ ናይጄሪያ እና ከናይጄሪያ የሚያደርገውን በረራውን ለማቆም የወሰነው በአገሪቱ ያለውን ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ መሆኑን አስታውቋል።
ኢሚሬትስ አየር መንገድ በአገሪቱ ሲሰጥ ለቆየው የአየር ትራንስፖርት አገለግሎቱ ከናይጄሪያ ማግኘት ያልቻለው 85 ሚሊዮን ዶላር እንዳለው አመልክቷል።
አየር መንገዱ ገንዘቡን ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ናይጄሪያ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር እንደሚቀንስ ለአገሪቱ አቪዬሽን ሚኒስቴር በደብዳቤ አስታውቆ ነበር።
በደኅንነት እና ለመንገደኞች በሚሰጠው ምቾች የ2022 የዓለማችን ምርጥ 20 አየር መንገዶች ውስጥ መካተት የቻለው ኤሚሬትስ፤ ነሐሴ 2014 አጋማሽ ላይ የበረራ ቁጥሩን ከመቀነሱ በፊት በሳምንት ለ11 ጊዜ ያህል ወደ ናይጄሪያ መዳረሻዎች ይበር ነበር።
ኤሚሬትስ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪ ላለመብረር መውሰኑን ተከትሎ መጉላለት ሊገጥማቸው የሚችሉ ደንበኖቹ የአየር ቲኬታቸውን በመሰረዝ ገንዘባቸውን ተመላሽ ማድረግ እንደሚችሉ አልያም ከሌሎች የአፍሪካ መዳረሻዎች መነሳት ወይም መብረር እንደሚችሉ አማራጭ ሰጥቷል።
ከኤሚሬትስ በተጨማሪ ሌሎች ግዙፍ አየር መንገዶች በአፍሪካ ግዙፍ ከሚባሉት መዳረሻዎች መካከል አንዷ ከሆነችው ናይጄሪያ ያላቸውን ገንዘብ ማንቀሳቀስ አለመቻላቸውን በመግለጽ ቅሬታ ያሰማሉ።
ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ወደ ናይጄሪያ የሚበሩ ሌሎች አየር መንገዶችም የኤሚሬትስን ውሳኔ ሊከተሉ ይችላሉ።
አየር መንገዶች በናይጄሪያ ማንቀሳቀስ ያልቻሉት የገንዘብ መጠን 600 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ተጠቅሷል።
በአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ የሆነችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ የውጭ ኩባንያዎች ላቀረቡት ምርትና አገልግሎት ከአገሪቱ በሚያውጡት የውጭ ምንዛሬ መጠን ላይ ገደብ ጥላለች።












