ምዕራባውያን መሪዎች የፑቲንን የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አደረጉ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ
ታትሟል

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ባለመ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ምዕራባውያን አገራት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለማስቆም ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ አደረጉ።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂርጂአ ሜሎኒ የፕሬዝዳንት ፑቲንን ቅድመ ሁኔታ “ፕሮፖጋንዳ” ብለው ከገለጹት በኋላ ዕቅዱ ዩክሬን “ከዩክሬን ለቅቃ መውጣት አለባት” የሚል ነው ብለዋል።

የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ስሎዝ ደግሞ የፑቲንን ቅድመ ሁኔታ “አምባገነናዊ የሰላም ጥሪ” ብለውታል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ደግሞ ከቅድመ ሁኔታው ፑቲን ጦርነቱን የማስቆም ፍላጎት እንደሌላቸው መረዳት ይቻላል ብለዋል።

ጦርነቱን ለማስቆም አልሞ ለሁለት ቀናት በስዊትዘርላንድ እየተካሄደ የሚገኘው ስብሰባ ሲጠናቀቅ አገራቱ በሚያወጡት የውሳኔ ሃሳብ ላይ የዩክሬን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ይጠይቃሉ። እንዲሁም ዩክሬንን በኒውክለር ጦር መሳሪያ ማሸበር ተቀባይነት የማይኖረው ተግባር ነው በሚል ይስማማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መሪዎቹ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቅድመ ሁኔታ አጥበቀው የተቹት፤ ፑቲን ከሁለት ቀናት በፊት በዩክሬን ላይ ለከፈቱት ዘመቻ ማብቂያ ይሆናል ያሉትን ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጡ በኋላ ነው።

ፑቲን የዩክሬን መንግሥት በከፊል በሩሲያ ከተያዙት አራቱ ክልሎች ማለትም ከዶኔስክ፣ ሉሃንስክ፣ ኼርሶን እና ዛፖሬዢያ ለቆ መውጣት አለበት ብለዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ጨምረውም የሰላም ስምምነቱ ከመጀመሩ በፊት ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የመሆን ፍላጎቷን ጨርሳ መተው አለባትም ብለዋል።

“ኪዬቭ በእነዚህ ቅደመ ሁኔታዎች ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ዝግጁ ስትሆን በእኛ በኩል ወዲያውኑ ተኩስ እንዲቆም እና ድርድር እንዲጀመር ትዕዛዝ እናስተላልፋለን” ብለዋል ፑቲን።

ይህን የፑቲንን ቅድመ ሁኔታ ዩክሬን እንደማትቀበል ቀድማ አስታውቃለች። በተመሳሳይ አሜሪካ ቅድመ ሁኔታው ተግባራዊ እንደማይደረግ ገልጻለች።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ የሆኑት አንድሪ ዬርማክ በስዊዘርላንድ እየተደረገ ያለው ስብሰባ የዩክሬን “ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑን አረጋግጧል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሩሲያ ባልተጋበዘችበት እንዲሁም ቻናይ ለመገኘት ፍቃደኛ ያልሆነችበት የስዊዘርላንዱ ስበሰባ ከ90 በላይ አገራት ተሳታፊ እየሆኑ ይገኛሉ።

በፑቲን የተስኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታ ላይ አስተያየት የሰጡት የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ፤ “ዩክሬን ከራሷ ግዛት እንድትወጣ መጠየቁ ጦርነት ለማስቆም የሚደረግ የድርድር አማራጭ ሆኖ አይታየኝም” ብለዋል።

የዩናትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በተመሳሳይ ከፑቲን የድርድር ቅድመ ሁኔታ የምንረዳው ሩሲያ ጦርነቱን በንግግር ለማስቆም ፍላጎት እንደሌላት ነው ብለዋል።

ሪሺ ሱናክ ጨምረውም በዚህ ጦርነት ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እያደረጉ የሚገኙ አገራት በታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ አገራቸው “ለዲፕሎማሲ ዕድል መስጠት” መፈለጓን እንዲሁም በጋራ ጥረት ጦርነቱን ማስቆም እንደሚቻል እምነት እንዳላቸው ለስበሰባው ታዳሚዎች ተናግረዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዲሁም የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ላይን ተሳታፊ ናቸው።