ሞሐመድ ሳላህ ሊቨርፑልን መሰናበት ይፈልጋል የሚባለው እውነት ነው? የኤሪክ ቴን ሃግ ጉዳይስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቼልሲ የሊድስ ዩናይትዱን ግብ ጠባቂ ማስፈረም እንደሚሻ ፉትቦል ኢንሳይደር የተባለው ጋዜጣ ይፋ አድርጓል።
የ23 ዓመቱ ፈረንሳዊ ኢላን ሜሊዬ በሌሎች ክለቦችም የሚፈለግ ቢሆንም ቼልሲ ግን አጥብቆ ይፈልገዋል ሲል ጋዜጣው አስነብቧል።
ሌላኛው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ኒውካስትል ዩናይትድ የባየር ሌቨርኩሰን የክንፍ መስመር ተጨዋች የሆነውን ሙሳ ዲያቢን ማስፈረም ይሻል።
'90ሚን' የተሰኘው የጀርመን የስፖርት ጋዜጣ እንደፃፈው የ23 ዓመቱ ብቻ ሳይሆን ሌላኛው የሌቨርኩሰን የግራ መስመር ተጫዋች ሚቼል ቤከር በኒውካስትል ይፈለጋል።
ሙሳ ዲያቢ በአርሰናል ዐይን ውስጥ ከገባ ቆየት ቢልም የሊጉ መሪዎች በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ ሃብታሞች ከተገዛው ኒውካስትል ጋር ይገዳደራሉ ማለት ከባድ ነው።
ዲያቢ 62 ሚሊዮን ፓውንድ ተገምቷል።
ሞሐመድ ሳላህ ሊቨርፑልን መልቀቅ ይፈልጋል የሚሉ ወሬዎች በስፋት መናፈስ ጀምረዋል።
ነገር ግን 90ሚን የሞሐመድ ሳላህን ወኪል ዋቢ አድርጎ ግብፃዊው አጥቂ በሊቨርፑል መቆየት ይሻል ሲል ጽፏል።
ሌላኛው የሊቨርፑል አጥቂ ብራዚላዊው ሮቤርቶ ፈርሚኖ ከክለቡ ጋር የገባው የውል ጊዜ እየተጠናቀቀ ቢሆንም፣ አውሮፓ ውስጥ መቆየት እንደሚፈልግ ፉትቦል ኢንሳይደር ዘግቧል።
ሊቨርፑል እና ፈርሚኖ የፈጸሙት ስምምነት በዘንድሮው የውድድር ዘመን መገባደጃ ያበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ውላቸውን ለማራዘም ከክለቡ ጋር ድርድር ላይ መሆናቸውን ሚረር አስነብቧል።
ምንም እንኳ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊሸጥ ቢሆንም፣ አሠልጣኙ ግን መቆየት እንደሚሹ ተነግሯል።
ባለፈው ክረምት የዩናይትድ አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ቴን ሃግ በክለቡ ትልቅ ለውጥ እያመጡ ነው ተብለው ይሞገሳሉ።
በኤሪክ ቴን ሃግ የሚመራው ማንቸስተር ዩናይትድ የዘንድሮው የሊግ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።
በፕሪሚዬር ሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዩናይትድ በአውሮፓ ሊግ እና በኤፍ ኤ ዋንጫ እየተፋለመ ይገኛል።
የኔዘርላንድ ጋዜጣ 'ሄት ሌተስት ኒውስ' ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ የአንደርሌክቱን ግብ ጠባቂ ማስፈረም ይፈልጋሉ ብሏል።
እንደጋዜጣው ከሆነ ሁለቱ ታሪካዊ ተቀናቃኝ ክለቦች የ20 ዓመቱን ባርት ቨርብሩገን ለማስፈረም እየተፎካከሩ ነው።
ሌላኛው የደች ጋዜጣ ዴ ቴሌግራፍ ማንቸስተር ዩናይትድ የአያክሱን ጋናዊ አጥቂ ሞሐመድ ኩዱስ ማስፈረም ቢፈልግም ተጫዋቹ ግን ትኩረቱ የደች ሊግ ዋንጫን ማንሳት ነው ብሏል።
የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋቾች ቲዬሪ ኦንሪ እና ፓትሪክ ቪዬራ የዩናይትድ ስቴትስ የወንዶች ብሔራዊ ቡድንን ለማሠልጠን እንደቋመጡ ያስነበበው ደግሞ ጎልዶትኮም ነው።
ፓትሪክ ቪዬር ከክሪስታል ፓላስ አሠልጣኝነቱ የተባረረው ባለፈው አርብ ነው።












