ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊውን በ46 ጥይት እንደመታው በአስክሬን ምርመራ ተረጋገጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሦስት ሳምንታት በፊት በአሜሪካዋ ኦሃዮ ግዛት በፖሊስ የተገደለው የ25 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ ወጣት 46 ጊዜ በጥይት መመታቱን በአስክሬኑ ላይ የተደረገ ምርመራ አረጋገጠ።
በአስከሬኑ ላይ ምርመራውን ያደረጉ ባለሙያዎች ጄይላንድ ዎከርን 46 ጥይቶች መትተውታል ወይም ጨርፈውት አልፈዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ዎከርን የገደለው የትኛው ጥይት እንደሆነ እና ፖሊስ በአጠቃላይ ምን ያህል ጥይት በወጣቱ ላይ እንደተኮሰ አለመታወቁን አመልክተዋል።
ይህ የአስክሬን ምርመራ ይፋ የተደረገው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወጣቱ ግድያ የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለጽ ኦሃዮ ግዛት ውስጥ በምትገኘው የአክሮን ከተማ ከተሰባሰቡ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።
የከተማዋ ባለሥልጣናት የከተማዋን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲሉ ትናንት ዓርብ ሐምሌ 08/2014 ዓ.ም. የሰዓት እላፊ ገደብ ጥለዋል።
ከሦስት ሳምንታት በፊት ከፖሊስ በተተኮሱበት ጥይቶች ተመትቶ ሕይወቱ ያለፈው ዎከር፤ ልቡ፣ ሳንባዎቹ እና የደም ማስተላለፊያ ቱቦዎቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አሁን ይፋ የተደረገው የአስክሬን ምርመራ ውጤት አሳይቷል።
የግዛቲቱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ዎከር የትራፊክ ሕግ ከተላለፈ በኋላ በፖሊስ እንዲቆም ሲጠየቅ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ፖሊስ ለ6 ደቂቃዎች ሲከታተለው ነበር ብለዋል። ፖሊስ እያሳደደው ሳለ ዎከር አንድ ጊዜ ተኩሶ እንደነበረም ተገልጿል።
ፖሊስ ይፋ ያደረገው ተንቀሳቃሽ ምስል፤ ፊቱ ላይ ጭምብል ያጠለቀው ዎከር እየሄደ ካለ መኪና በተሳፋሪው በር በኩል ወርዶ፣ በአንድ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ውስጥ ከለላ ለማግኘት ሲሞክር ፖሊሶች ከተያየ አቅጣጫ ተኩስ ከፍተውበታል።
ዎከር ፖሊሶች ከተለያያ አቅጣጫ ተኩስ ሲከፍቱበት መሳሪያ ይዞ እንዳልነበረ በመጥቀስ በመጥቀስ የተወሰደበት እርምጃ አግባብ አይደለም ሲሉ ቤተሰቦቹ ፖሊሶቹን ወቅሰዋል።
የአካባቢው የፖሊስ አባላት ማኅበር ግን የፀጥታ አስከባሪዎቹ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል በሚችል ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ስለተገነዘቡ በወሰዱት ሥልጠና መሠረት እርምጃ ወስደዋል ሲል አባላቱን ተከላክሏል።
የኦሃዮ ግዛት በጉዳዩ ላይ የሚያደርገው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ዎከር ላይ ተኩስ ከፍተው የገደሉት 7 ነጭ እና አንድ ጥቁር የፖሊስ አባላት ጥቅማቸው ተከብሮ አስገዳጅ እረፍ ላይ እንዲቆዩ አድርጓል።
ይሁን እንጂ ክስተቱን የኦሃዮ ግዛት ሳይሆን የፌደራል መንግሥቱ እንዲመረምረው ለአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው።












