ቱርክ በርዕደ መሬቱ ከፈረሱ ህንጻዎች ጋር በተያያዘ 180 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዋለች

ታትሟል

በቱርክ ባጋጠመው ርዕደ መሬት ከፈረሱ ህንጻዎች ጋር በተያያዘ 180 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግሥት አስታወቀ።

በርዕደ መሬቱ ከወደሙ ህንጻዎች ጋር ተያይዞ ከ600 በላይ ግለሰቦችም ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።

የሃገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ቤኪር ቦዝዳግ የግንባታ ተቋራጮች እና የህንጻ ባለቤቶችን ጨምሮ 184 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አስታውቀዋል።

በሃገሪቱ የሰፈነው ሙስና እና በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ የሚታየው ክፍተት የህንፃዎችን ደህንነት ሊያስጠብቅ እንዳልቻለ ለዓመታትም ባለሙያዎችም ሲያስጠነቅቁ ነበር።

በቱርክ እና ሩሲያ ባጋጠሙ ርዕደ መሬቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በልጧል።

ሚኒስትሩ 7.8 ሬክተር ስኬል ርዕደ መሬትና ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከፍተኛ መንቀጥቀጥ ባስተናገደችው የደቡብ ምስራቅ ግዛት ላይ ሆነው ነው የቴሌቪዥን መግለጫውን የሰጡት።

መግለጫቸው መንግሥታቸው የጀመረውን ምርመራ መጠነ ሰፊነት ያሳየ ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በፊት 113 የእስር ማዘዣዎች መውጣታቸውን ባለስልጣናቱ ገልጸው ነበር።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ርዕደ መሬቱ ከተከሰተባቸው ከተሞች የአንዱ ከንቲባ እንደሚገኙበት የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ርዕደ መሬቱን ተከትሎ በቱርክ ከ160 ሺህ ህንጻዎች በላይ ወድመዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በህንጻዎቹ ላይ የነበረው ጉድለት የርዕደ መሬቱን ጉዳት አክፍቶት ይሆን የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና አንዳንድ የግንባታ ባለሙያዎች የፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አስተዳደር የግንባታ ደንቦችን ተግባራዊ ባለማድረግ እና ለአደጋው ኃላፊነቱን ላለመውሰድ እየሞከረ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

ግንባታዎችን ለማበረታት በሚል ለርዕደ መሬት በተጋለጡ ግዛቶች ጨምሮ የመንግሥት ፖሊሲ የግንባታ ደንቦችን ለጣሱ ተቋራጮች ፍቃድ ሰጥቷል በማለት ይተቻሉ።

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ያሉ ድክመቶችን ቢያምኑም ለደረሰው መጠነ ሰፊ አደጋ እድልን ተጠያቂ አድርገዋል።

"እንዲህ አይነት ነገሮች ሁልጊዜም ይከሰታሉ። ይህ እጣ ፈንታ ነው” ሲሉም በቅርቡ በርዕደ መሬቱ የተጠቁ ስፍራዎችን በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል።

ሃገሪቱ ምርጫ ለማድረግ እየተቃረበች ባለችበት ወቅት ኤርዶጋን ከ20 ዓመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ የወደፊት እጣ ፈንታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ስለ አንድነት እያቀረቡት ያለው ተማጽኖም ብዙም ሰሚ አላገኘም።