ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከፍተኛ ፉክክርና ጥቃቶችን ያስተናገደው የናይጄሪያው ምርጫ
ናይጄሪያ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ፉክክር የታየበትን ምርጫ ቅዳሜ፣ የካቲት 18/2015 ዓ.ም አድርጋለች።
የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት በዚህ ምርጫ ድምጽ የመስጠት ሁኔታ መዘግየት እና በአንዳንድ አካባቢዎችም በታጠቁ ግለሰቦች ጥቃት ደርሷል።
ከአውሮፓውያኑ 1999 ወታደራዊ አገዛዝ ማክተሚያ በኋላ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት የዘንድሮው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የድምጽ ቆጠራም እየተካሄደ ነው።
በምርጫው በርካታ ወጣቶችና የመጀመሪያ መራጮች ገና ጎህ ሳይቀድ ነበር ድምጻቸውን ለመስጠት የመጡት።
አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች መጓተት፣ የምርጫ ከረጢቶች መነጠቅ እና ጥቃቶችንም አስተናግደዋል ተብሏል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ አንዳንድ መስተጓጎሎችን ሪፖርት ማድረጋቸውን ተከትሎም ውጤቱን አከራካሪ ሊያደርገው እንደሚችልም ተገምቷል።
87 ሚሊዮን ህዝብ መራጭ የሆነበት የናይጄሪያው ምርጫ በአፍሪካ ከፍተኛው የዲሞክራሲ እንቅስቃሴም እንደሆነም ተቆጥሯል።
ወታደራዊው አገዛዝ አክትሞ የመድብለ ፓርቲ ከተመሰረተ በኋላ ያለፉት 24 አመታት የናይጄሪያ ፖለቲካ በሁለት ፓርቲዎች ማለትም በገዥው ኤፒሲ እና ፒፒዲ የበላይነት የተያዘ ሆኖ ቆይቷል።
ነገር ግን ፕሬዚዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪን ለመተካት በሚደረገው የዘንድሮው ምርጫ በበርካታ ወጣቶች የሚደገፈው የሌበር ፓርቲ ፒተር ኦቢ መድረኩን ተቀላቅለዋል።
በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምጽ በመቆጠር ላይ ሲሆን ይህም ተሰብስቦ በዋና ከተማዋ አቡጃ ወደሚገኘው የምርጫ ኮሚሽን ዋና ቢሮ ይላካል።
የመጨረሻው ውጤት ከመጪው ማክሰኞ በኋላ ይፋ ይሆናል።
ቅዳሜ እለት የምርጫ አስፈጻሚው ማህሙድ ያኩቡ በሰጡት መግለጫ በምርጫ ጣቢያዎች ላይ በድምጽ አሰጣጥ ላይ የታየውን መዘግየት ጠቅሰው ይቅርታ ጠይቀዋል። ማንኛውም ድምጹን ለመስጠት ወረፋ ይዞ ያለ ግለሰብም የምርጫ ድምጽ ይሰጣል በማለት የምርጫ ጣቢያዎች በይፋ ይዘጋሉ ከተባለበት ሰዓትም መራዘሙን አስታውቀዋል።
በትልቋ ከተማ ያሉ ሌጎስ የነበሩ መራጮች የምርጫ ጣቢያዎች ከተዘጉ ከአራት ሰዓታት በኋላ በሌኪ ከተማ ዳርቻ የሚገኝ ጣቢያ ላይ አስፈፃሚዎች ሲደርሱ በርካቶች ደስታቸውን ገልጸዋል።
“ናይጄሪያዊ እንደመሆኔ ምንም ነገር ሊያጋጥመኝ እንደሚችል እጠብቃለሁ። ስለዚህ ስልኬ ባትሪው ቢሞት እንኳን በሚል ፓወር ባንክ እና ውሃ ይዤ መጥቻለሁ። አስፈጻሚዎች እስኪመጡ ድረስ ጠብቄ እመርጣለሁ” ስትል የመጀመሪያ መራጭ የሆነችው ኤዲት ለቢቢሲ ተናግራለች።
የምርጫው ዕለት በአብዛኛው ሰላማዊ ቢሆንም በሌጎስ አንዳንድ ጥቃቶችና የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች መዘረፉ ሪፖርት ተደርጓል።
አንዳንድ መራጮች ድምጻቸውን ለመስጠት በተሰለፉበት አካባቢ ጥቃት እንደደረሰባቸውና እንደተባረሩም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
በሌሎች ቦታዎች ደግሞ መራጮች የተወሰኑ ዕጩዎችን እንዲመርጡ ወይም የምርጫ ማዕከሎችን ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
በደቡባዊ ዴልታ እና በሰሜናዊ ካትቲሳ ግዛቶች ውስጥ የታጠቁ ታጣቂዎች አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ያኩቡ ተናግረው፣ የመራጮች ካርድ ማረጋገጫ ማሽኖችም ተወስደዋል ብለዋል።
እነዚህ ማሽኖች መተካታቸውንና የድምጽ መስጠቱም ስርዓት እንዲቀጥል የጸጥታ ጥበቃው በከፍተኛ ሁኔታ መጠናከሩን ገልጸዋል።
ነገር ግን በነዳጅ ዘይት በበለጸገችው ደቡባዊ ባዬልሳ ግዛት ውስጥ በሚገኙ 141 የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ መስጠት በመቋረጡ ምክንያት ለእሁድ መራዘሙንም ተናግረዋል።
በሰሜን ምስራቅ ቦርኖ ግዛት ታጣቂዎች በግዎዛ አካባቢ ተራጫ ጫፍ ላይ በምርጫ መኮንኖች ላይ ተኩስ ከፍተው በርካታ ባለስልጣናትን አቁስለዋል ብለዋል።
ከምርጫው ቀደም ብሎ ተከስቶ የነበረው የአዲሱ ገንዘብ እጥረት ባስከተለው ሁኔታ ከፍተኛ ቁጣና በባንኮች ላይ ሁከትና ጥቃትን አስከትሏል።
አዲሶቹ ገንዘቦች አገሪቱ ያጋጠማትን የዋጋ ግሽበት ለመቅረፍ እንዲሁም የመራጮችን ድምጽ የሚገዙ ፖለቲከኞችን ለመከላክል ነበር የተዋወቁት። በምርጫው ዋዜማ አንድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ወደ 500 ሺህ ዶላርና ገንዘቡ የሚሰጣቸውን ሰዎች ዝርዝር ይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
የሃገሪቱ ቀጣይ ፕሬዚዳንት የገንዘብ ማሻሻያውን፣ እየተንኮታኮተ ያለውን ኢኮኖሚ፣ ከፍተኛ የወጣቶች ስራ አጥነት እና ባለፈው ዓመት 10 ሺህ ሰዎች የተገደሉበትን የጸጥታ ችግር መጋፈጥ አለባቸው።