ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ምን ማለት ነው? ምን ምን ጥቅሞች ይሰጣል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላላፉት አራት ተከታታይ ዓመታት የፕላቲኒየም ደረጃ ግብር ከፋይነታቸውን ላስቀጠሉ ግብር ከፋዮች ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው መፈቀዱን ተናግረዋል።
7ኛው ዙር የግብር ከፋዮች የዕውቅና መርሃ ግብር እና የታክስ አስተዳደሩን ያዘምናሉ የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን ይፋ የማድረግ መርሃ ግብር ጠ/ሚ ዐቢይ በተገኙበት ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ. ም. ተከናውኗል።
ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ በተካሄደው የግብር ከፋዮች የዕውቅና መርሃ ግብር በፕላቲኒየም ደረጃ 105፣ በወርቅ ደረጃ 245፣ በብር ደረጃ 350 በአጠቃላይ 700 ግብር ከፋዮች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ግብር ከፋዮቹ በዕውቅና መርሃ ግብር የተካተቱት ለታክስ ባላቸው ተገዢነት እና ያደረጉት አስተዋጽኦ ታይቶ መሆኑ ተገልጿል።
30 ግብር ከፋዮች ለተከታታይ አራት ዓመታት የፕላቲኒየም ግብር ከፋይነት ደረጃቸውን ይዘው በማስቀጠላቸው የልዩ ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል።
ላለፉት ተከታታይ አራት አመታት የፕላቲኒየም ግብር ከፋይነት ደረጃቸውን ይዘው ያስቀጠሉ በመሆናቸው ግብር ከፋዮች በልዩነት ዕውቅና አግኝተዋል።
በልዩነት ዕውቅና ለተሰጣቸው 30 የፕላቲኒየም ደረጃ ግብር ከፋዮች የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው መወሰኑን ጠ/ሚ ዐቢይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 30 ልዩ ተሸላሚዎች ባለቤቶቻቸው ኢትዮጵያዊያን ከሆኑ ለድርጅቱ ባለቤት ወይም ሲኢኦ እንደ ድርጅቱ ምርጫ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
"በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለሥራ ሲንቀሳቀሱ ቪዝን ጨምሮ ላለው ማንኛውም ነገር መስተጓጎል እንዳይገጥማቸው፣ልዩ የፕላቲኒየም ተሸላሚዎች፤ ባለቤት ወይም ሲኢኦ፣ እንደ ኩባንያው ምርጫ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ሰጥተን እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የሚወሰዱ ይሆናል።"
በተጨማሪም በብር እና በወርቅ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑ ግብር ከፋዮች "ምርጥ ዜጎች ስለሆኑ" በኢትዮጵያ አየር መንገድ በቪአይፒ ተርሚናል እንዲስተናገዱ ተወስኗል ብለዋል።
ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ምንድን ነው?
ዲፕሎማቲክ ፓስፖርቶች የሚሰጡት ለይፋዊ የመንግሥት ሥራ በሌላ አገር ተመድበው አገራቸውን ለመወከል ለሚሄዱ የመንግሥት ዲፕሎማቶች ነው።
ዲፕሎማቶቹ የሚመደቡት በአገሪቱ መንግሥት ሲሆን ከተመደቡበት አገር ጋር አገራቸውን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መስክ ይወክላሉ።
የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የሚይዝ ግለሰብ በሚንቀሳቀስበት አገር የውጭ መንግሥት ተወካይ እንደሆነ ይቆጠራል።
ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የሚይዝ ሰው የአገሩን መንግሥት መመሪያዎች የመከተል ኃላፊነት አለበት።
አንዳንድ ጊዜ እንደ አገሪቱ ሕግ የሚወሰን ቢሆንም የዲፕሎማት ቤተሰቦችም ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ይሰጣቸዋል።
ይሁን እንጂ አንድ ባለሥልጣን የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዳገኘ ቤተሰቡም ይህንን ለማግኘት ወዲያውኑ ብቁ ይሆናል።
ፓስፖርቱን የያዘው ግለሰብ የማይጓዝ ከሆነ ለሰጠው አካል መመለስ ይኖርበታል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሕገ መንግሥት እና ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የጦር ጄነራሎች እና አድሚራሎች የቀድሞ እና የአሁን አገር መሪዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ወዘተ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ሊያገኙ ይችላል።
ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዘ ግለሰብ ዓለም አቀፍ ጉዞዎች በሚያደርግበት ወቅት የሚያልፋቸው የጉዞ ደንቦች ያሉ ሲሆን መደበኛ ፓስፖርት የሚይዙ ሰዎች የሌላቸው ዲፕሎማቲክ ከለላ ያገኛል።
ይህ ግን እንደሚጓዝበት ወይም እንደሚኖርበት አገር የኢሚግሬሽን መመርያ እና ደንብ የሚወሰን ይሆናል።
ዲፕሎማቲክ ዋስትና ያላቸው እና የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የሚይዙ ግለሰቦች ያለ መከሰስ እና በሚቀመጡበት አገር ከታክስ ነጻ የመሆን ዕድሎችን ያገኛሉ።
የተወሰኑ አገራት ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለያዙ ግለሰቦች ያለ ቪዛ እንዲገቡ እና እንዲወጡ በማድረግ የኢሚግሬሽን ፍተሻን ያቃልላሉ።
ይሁን አንጂ ይህ የሚሠራው ዲፕሎማቱ አገሩን እንዲወክል በተፈቀደለት አገር ውስጥ ብቻ ነው።
ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የሚይዙ ግሰቦች በአየር ማረፊያዎች ያለውን አሠራር በማለፍ ያለ ምንም ውጣ ውረድ የመንቀሳቀስ ዕድል ያገኛሉ።
ይህም ማለት ሁሉንም ነገር ይጥሳል ማለት ሳይሆን እንደ ሻንጣ ፍተሻ እና ማንነት የማረጋገጥ ስራዎች በአየር መንገድ ውስጥ የሚቆዩበትን ሰዓት አያረዝመውም ማለት ነው።
በተጨማሪም ሌሎች አገሮች በቪየና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስምምነት (VCDR) መሠረት በውጭ ሚሲዮን እና በአገር ውስጥ ለመጓዝ ለዲፕሎማቲክ ባለሥልጣኑ መግቢያ መስጠት አለባቸው።
ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ ግለሰቦች በአየርም ሆነ በየብስ ወደ ሌላ አገር ሲሄዱ ከታክስ ነጻ የሆነ ዕድል ተጠቃሚ ናቸው።
መንግሥታት ይገባቸዋል ለሚሏቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት መስጠት የሚችሉ ሲሆን ለግል ጥቅም ወይንም አለ አግባብ ጥቅም ላይ ማዋል ከአስተናጋጇ አገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ያስከትላል።
የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት መኖሩ አስተናጋጁ አገር ካልተቀበለው በቀር ያለመከሰስ መብትን ወድያውኑ አይሰጥም።
መንግሥት ለልዩ ልዑክ፣ ለሰላም አምባሳደር፣ የአገርን ፍላጎት ለሚወክሉ የባህል አምባሳደሮች እንዲሁም ለይፋዊ ልዑካን ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ሊሰጥ ይችላል።
ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የምትሰጠው ለማን ነው?
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ሦስት ዓይነት ፓስፖርቶችን ትሰጣለች።
ይህም መደበኛ፣ ዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት በመባል ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የምትሰጥበት መስፈርት በአዋጅ ተደንግጎ ተቀምጧል።
በዚሁ አዋጅ መሠረት የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የሚሰጣቸው በውጭ አገር በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቋሚ መልዕክተኛ ወይም ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ለሚመደቡ አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ወኪሎች፣ አታሼዎች የቆንስላ ወኪሎች እና የትዳር አጋሮቻቸው ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል በጉባዔ ወይንም በስብሰባ ለመሳተፍ ወይም ለሌላ የመንግሥት ሥራ ወደ ውጭ አገር ለሚሄዱ ደረጃቸው ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ ለሚወሰን መልዕክተኞችም የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ይሰጣል።
ከዚህ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ውጭ አገር ለሚሄዱ ደረጃቸው ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ ለሚወሰን የመንግሥት ባለሥልጣኖች የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ባለቤት ይሆናሉ።
በዓለም አቀፍ እና በአህጉራዊ ደረጃ ለሚሠሩና የዲፕሎማቲክ ደረጃ ላላቸው ኢትዮጵያውያን እና የትዳር አጋሮቻቸው እንዲሁም ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ከፍተኛ ክብር ለሚሰጣቸው ሰዎች የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ይሰጣል።
የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዲሰጥ ግን ጉዳዩ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት ወይም እንደ ሁኔታው አመልካቹ ራሱ ለሚኒስቴሩ በሚያቀርበው ማመልከቻ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለማሰጠት የሚያበቃው ምክንያት በግልጽ መጠቀስ አለበት።
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት የሚሰጣቸው የፖስፖእርት ዓይነቶች የተለያየ የአገልግሎት ዘመን አላቸው።
በዚህም የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የሚሰጣቸው ሰዎች ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ ከሆነ ፓስፖርቱ የ10 ዓመት የአገልግሎት ዘመን ሲኖረው እስከ 25 ዓመት ድረስ ለሆኑ ደግሞ አምስት ዓመት ብቻ የሚያገለግል ይሆናል።