ከሥራ የታገዱት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኛ አደገኛ ዕፅ ሲጠቀሙ የሚያሳይ ቪድዮ ወጣ

ዋና አርቢትር ዴቪድ ኩት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእንግሊዝ እግር ኳስ ዳኞች ማኅበር የፕሪሚዬር ሊጉ ዳኛ ላይ የቀረበውን ክስ “በአንክሮ እንደሚያጤነው” አሳውቋል።

ፒጂኤምኦኤል በተባለ ምሕፃረ ቃሉ የሚታወቀው የዳኞች ማኅበር እንዳለው በሊጉ ዳኛ ዴቪድ ኩት ላይ የቀረበው ክስ በቀልድ የሚታለፍ አይደለም።

ዘ ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ረቡዕ ባወጣው ቪድዮ ላይ ዳኛው ኮኬይን የተባለውን ዕፅ ሲስቡ ይታያሉ። ጋዜጣው ዴቪድ ኩት ናቸው ብሎ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ ላይ የለጠፈው ቪዲዮ ሰውዬው በተጠቀለለ የአሜሪካ ዶላር ከጠረጴዛ ላይ ዕፁን ሲስቡ ያስመለክታል።

ኩት ይህን ያደረጉት በአውሮፓ ዋንጫ ሰሞን ነው ተብሏል። ሰውዬው የአውሮፓ ዋንጫን ለመምራት ከተመረጡ ዳኞች መካከል ነበሩ።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊጉ ዳኛ በያዝነው ሳምንት መባቻ ከሥራቸው የታገዱት ሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ እና የቀድሞው አሰልጣኝ ዩርገን ክሎፕን ሲዘልፉ የሚያሳይ ቪድዮ ከተሰራጨ በኋላ ነው።

የዳኞች ማኅበር ቃል አቀባይ “የቀረቡትን ክሶች እናውቃቸዋለን። ክሶቹን በአንክሮ የምናጤናቸው ይሆናል” ብለዋል።

ዴቪድ ኩት ከሥራቸው ታግደው ሙሉ ምርመር እየተደረገባቸው እንደሆነ የዳኞች ማኅበር አስታውቋል።

“ዋናው እና ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር የዴቪድ ሁኔታ ነው። የትኛውንም ዓይነት እርዳታ ልናደርግለት ዝግጁ ነን። በአሁኑ ወቅት ከዚህ ያለፈ አስተያየት መስጠት አንችልም” ብሏል።

ዘ ሰን ጋዜጣ እንደዘገው ቪዲዮዎቹ የዳኛው ጓደኛ ለሆኑ ግለሰብ በተደጋጋሚ የተላኩ ናቸው።

ቢቢሲ ቪድዮው ላይ የሚታዩት ግለሰብ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊጉ ዳኛ ስለመሆናቸው በግሉ ማጣራት አልቻለም።

ቢቢሲ ዴቪድ ኩት በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቧል።

በሌላ በኩል የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ዩኤፋ ትክክለኛው ቪድዮ ከተገኘ በኋላ አርቢትሩ ከሥራቸው ለታገዳቸውን ቢቢሲ ስፖርት አረጋግጧል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ኩት በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ የሀገራት ጨዋታዎች መታገዳቸውን አሳውቋል።

የአውሮፓ አርቢትሮች ኮሚቴ ደግሞ ዳኛው ላልተወሰነ ጊዜ መታገዳቸውን ገልጿል።

የ42 ዓመቱ ኩት ባለፈው ቅዳሜ ሊቨርፑል አስተን ቪላን 2-0 ሲረታ የመሐል ዳኛ ነበሩ። በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አሉ ከሚባሉ እና ልምድ ካላቸው ዳኞች መካከል ሲሆኑ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ የፕሪሚዬር ሊጉ ዳኛ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኞች የትኛውን ክለብ እንደሚደግፉ ለዳኛው አስተዳዳሪው ማኅበር የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።

ኖቲንግሀም ከተባለው ሥፍራ የመጡት ዴቪድ ኩት ኖትስ ካውንቲ የተባለው ቡድን ደጋፊ ሲሆኑ የኖትስ እንዲሁም በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወተው ኖቲንግሀም ፎረስት ጨዋታዎችን መዳኘት አይችሉም።