አሜሪካዊቷ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች በሩሲያ የዘጠኝ ዓመት እስር ተፈረደባት

ብሪትኒ ግሪነር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሩሲያ አሜሪካዊቷን ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግሪነር ለመልቀቅ ስምምነት ላይ እንድትደርስ አሜሪካ ጠየቀች።

አደንዛዥ እጽ ይዛ ወደ ሩሲያ በመግባቷ የታሰረችው ብሪትኒ፣ በሩሲያ ፍርድ ቤት የዘጠኝ ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።

ሀለት ጊዜ የኦሎምፒክ ባለድል የሆነችው ቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ የካናቢስ ዘይት ይዛ መገኘቷን በፍርድ ቤት አምናለች።

የዋይት ሀውስ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፣ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ለመደራደር የምትችልበት የስምምነት ሰነድ እንዳዘጋጀች ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት፤ አሜሪካ ብሪትኒን በሩሲያዊው የመሣሪያ አዘዋዋሪ ልትለውጣት ትችላለች።

“የሞት ነጋዴው” እየተባለ የሚጠራው ቪክተር ቦውት በአሜሪካ የ25 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

የእስረኛ ልውውጡ ይሄንን መሣሪያ አዘዋዋሪ በቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ እንዲሁም በቀድሞው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ፖል ዌላን የሚቀይር ነው።

የአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አየርላንድ ፓስፓርት ያለው ግለሰቡ፣ በስለላ ተከሶ 16 ዓመት እስር በሩሲያ ፍርድ ቤት ተፈርዶበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዋይት ሀውስ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን፤ ሁለቱ አሜሪካውያን ያለአግባብ እንደታሰሩና መለቀቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

“ያቀረብነውን የስምምነት ሐሳብ ከሳምንታት በፊት መቀበል ነበረባቸው” ብለዋል።

ሮይተርስ እንደሚለው፣ ሩሲያ ስምምነቱን ያልተቀበለችው ጀርመን እስር ቤት ያለው ቫዳም ክራስኮቭ በእስረኛ ልውውጡ እንዲካተት ስለምትፈልግ ነው።

የ31 ዓመቷ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ “ስህተት መሥራቴን አምናለሁ። ሕግ ለመጣስ ብዬ አልነበረም” ብላለች።

ምርጥ ከሚባሉ ተጫዋቾች አንዷ ስትሆን ወደ ሩሲያ ያቀናችው ለቅርጫት ኳስ ጨዋታ ነበር።

አውሮፕላን ማረፊያ ሳለች ሻንጣዋ ውስጥ የካናቢስ ዘይት ተይዞ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለችው።

ታስራ ብዙም ሳይቆይ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ተነሳ።

ብሪትኒም በአሜሪካ እና በሩሲያ የዲፕሎማሲ ሽኩቻ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች።

ጠበቆቿ ለሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚሉ ገልጸዋል።

የብሪትኒ ቡድን ፊኒክስ ሜርኩሪ፣ ኮኒክቲክት ሰን ቡድንን ሲገጥም ለብሪትኒ ያለውን ድጋፍ ለማሳየት ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾቹ ለ42 ሰከንድ በጥሞና አሳልፈዋል።

መታሰቢያነቱ ብሪትኒ ለምትለብሰው 42 ቁጥር መለያ ነው።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፍርድ ቤቱን ብይን “ተቀባይነት የሌለው” ብለውታል።

“ሩሲያ በአፋጣኝ ለቃት ብሪትኒ ከባለቤቷ፣ ከጓደኞቿ፣ ከቡድን ጓደኞቿና ከወዳጆቿ ጋር እንድትቀላቀል እጠይቃለሁ” ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን “ሩሲያም ትሁን ሌሎች አገራት ያልተገባ እስር የሚፈጽሙ ከሆነ ወደተለያዩ አገራት እየሄዱ የሚሠሩ ሰዎች ደኅንነት ስጋት ውስጥ ይወድቃል” ብለዋል።

ብሊንከን ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት በስልክ ተነጋግረዋል።

አሁን ሁለቱም ለደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ውይይት ካምቦዲያ ይገኛሉ።