ጀርመን የጋዝ አቅርቦትን በሬሽን ለማድረግ ተቃርባለች ተባለ

ታትሟል

ጀርመን ከሩሲያ የምታገኘው የጋዝ አቅርቦት በመቀነሱ ጋዝን በሬሽን እንዲቀርብ ለማድረግ እንደተቃረበች ተነገረ።

የኢኮኖሚ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው አገሪቷ ያጋጠማትን የጋዝ እጥረት ለመፍታት የአስቸኳይ ጊዜ ዕቅድ አካል የሆነውን ‘የማንቂያ’ እንቅስቃሴ ጀምራለች።

ይህ ጀርመንን የገጠማት የኃይል አቅርቦት ችግር በዩክሬን ወረራ ምክንያት በአውሮፓ ኅብረት እና በሩሲያ መካከል ያለው ፍጥጫ አካል ነው።

የጀርመን ኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሃቤክ፣ ሩሲያ ጋዝን ከአውሮፓ ኅብረት ለተጣለባት ማዕቀብ ምላሽ ለመስጠት እንደ “ጦር መሣሪያ” ተጠቅማለች ብለዋል።

ሚኒስትር ሃቤክ “ራሳችንን ማታለል የለብንም። የጋዝ አቅርቦትን ማቋረጥ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በእኛ ላይ የሰነዘሩት ኢኮኖሚያዊ ጥቃት ነው” በማለትም ጀርመናውያን የጋዝ ፍጆታቸውን መቀነስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

“የደኅንነት ስጋትን፣ የዋጋ ንረትን መፍጠር እና እኛን እንደ ማኅበረሰብ መከፋፈል የፑቲን ስትራቴጂ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህንን ነው እየታገልን ያለነው” ሲሉም አክለዋል።

ለጀርመን ኢንደስትሪዎች የጋዝ አቅርቦትን በፈረቃ የማድረግ ፍላጎት እንደማይኖር ተስፋ እንደሚያደርጉ የገለጹት ሚኒስተሩ፣ ነገር ግን "ይህንን ካሉ አማራጮች ውጪ ለማድረግ አልችልም” ብለዋል።

ጀርመን የጋዝ አቅርቦት መቆራረጥና በአገሪቷ የጋዝ ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ ካስቀመጠቻቸው ሦስት የአስቸኳይ ጊዜ ዕቅዶች ወደ ሁለተኛው ተሸጋግራለች።

የጀርመን መንግሥት የጋዝ ማጠራቀሚያዎችን ለመሙላት 15 ቢሊየን ዩሮ ብድር እሰጣለሁ ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ትላልቅ የቢዝነስ ተቋማት የጋዝ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ እና ለኢንደስትሪዎች ጋዝ በጨረታ መሸጥ እንደሚጀምር ገልጿል።

አገሪቷ ወደ ሁለተኛው ደረጃ የአደጋ ጊዜ ዕቅድ መሸጋገሯ፣ የአቅርቦት መቆራረጡንና ሌሎች አማራጮችን በመፈለግ ሁኔታውን ለማጣጣም የሚደረገው በዘርፉ በተሰማሩ የተለያዩ ተቋማት ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።

ሆኖም አገሪቷ ምንም እንኳን በደረጃ ሁለት የአደጋ ጊዜ ዕቅድ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚቻል ቢሆንም መገልገያዎች በከፍተኛ ዋጋ ለደንበኞች እንዳይሸጡ አድርጋለች።

የጋዝ ኩባንያዎችም በአስቸኳይ ጊዜ ዕቅዱ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ አቅርቦትን ማረጋገጥ ነበረባቸው። የጋዝ አቅርቦት ተቋማትም ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ለኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሪፖርት ሲያደርጉ ነበር። የኤሌክትሪክ አስተላለፊዎችም የኃይል አቅርቦት ዘላቂነትን ማረጋገጥ ነበረባቸው።

መንግሥት ጣልቃ የሚገባው በሦስተኛው ደረጃ የአደጋ ጊዜ ዕቅድ ላይ ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት መቆራረጥ ሲኖር እና ገበያው ሊቋቋመው በማይችልበት ወቅት ነው።

በሦስተኛው ደረጃ የአደጋ ጊዜ ዕቅድ ለኢንደስትሪዎች አቅርቦት የተገደበ ሲሆን መኖሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ሌሎች ወሳኝ ተቋማት ጋዝ ማግኘታቸውን ግን ይቀጥላሉ።

ሐሙስ ዕለት የአውሮፓ ኅብረት የአየር ንብረት ፖሊሲ ኃላፊ ፍራንስ ቲመርማንስ እንዳሉት አስራ ሁለት የኅብረቱ አገራት ከሩሲያ የሚገባው ጋዝ በመቋረጡ ችግር ላይ ወድቀዋል።

ሩሲያ ባለፈው ሳምንት የቁሳቁስ ችግርን ምክንያት በማድረግ በኖርድ ስትሪም 1 የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር በኩል የምታቀርበውን ጋዝ 40 በመቶ ቀንሳለች። ይህም ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች አገራትን ለችግር ዳርጓል።

ሩሲያ አዲስ ያቀረበችውን የጋዝ ክፍያ ሥርዓት ባለማክበራቸውም ለፖላንድ፣ ለቡልጋሪያ፣ ለኔዘርላንድስ፣ ለዴንማርክ እና ለፊንላድ የምታቀርበውን ጋዝ አቋርጣለች።

በኢንቨስቴክ የነዳጅ እና ጋዝ ምርምር ኃላፊ ናታን ፓይፐር፣ ከሩሲያ ወደ አውሮፓ የሚተላለፈው የጋዝ አቅርቦት ላይ በቀጣይ ሊኖር የሚችለው እገዳ “እጅግ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

በበጋ ወራት የተስተጓጎለው የጋዝ አቅርቦት እምብዛም አስጨናቂ አይደለም። ክረምቱ ሲቃረብ ግን ሰዎች ተጨማሪ ማሞቂያ ስለሚያስፈልጋቸው ሁኔታው ሊባባስ ይችላል ብለዋል ናታን።

ጀርመን ጋዝን በፈረቃ ማከፋፈል አለባት የሚለው እየታየ ያለ ጉዳይ ቢሆንም፣ በክረምት ወቅት የጋዝ ዋጋ ከጨመረ ኢንደስትሪዎች የጋዝ አጠቃቀማቸው የተቆጠበ ባለመሆኑ በራሳቸው ጊዜ ፈረቃ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም ኃላፊው አክለዋል።