ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን ተከታዮች ቁጥር ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሰራሁ ነው አለ
የዓለማችን ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ባለቤት የሆነው ሜታ፣ በዋነኛው የትስስር መድረኩ ፌስቡክ ላይ ባልተገለጸ ሁኔታ የተከሰተውን የተጠቃሚዎች ተከታዮች ቁጥር መቀነስን ለማስተካከል እየሰራ መሆኑን ለቢቢሲ ገለጸ።
ሜታ ይህንን የገለጸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተከታዮቻቸው ቁጥር በድንገት ማሽቆልቆሉን ተከትሎ በማኅበራያ ሚዲያ ገጾች ላይ መገጋገሪያ ከሆነ በኋላ ነው።
በኢትዮጵያ እና በተቀረው ዓለም የሚገኙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ምክንያቱን ባላወቁበት ሁኔታ የተከታዮቻቸው ቁጥር መቀነሱን ሲገልጹ ነበር።
የተከታዮቻቸው ቁጥር ከቀነሰባቸው የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መካከል የሜታ መስራቾች ከሆኑት መካከል አንዱ እና የድርጅቱ መሪ የማርክ ዛከርበርግን ጨምሮ በሚሊዮኖች ተከታይ የነበራቸው ተጠቃሚዎች ይጠቀሳሉ።
ኩባንያው የተጠቃሚዎች የተከታዮች ቁጥር ላይ ለውጥ መከሰቱን እንደሚያውቅ ገልጾ፤ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ለቢቢሲ ገልጿል።
ሜታ የተከታዮች ቁጥር መለዋወጥን በተመለከተ ምን እንደተፈጠረ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል።
“ሁኔታዎች ወደነበሩበት ለመመስ በተቻለ ፍጥነት እየሰራን እንገኛለን” ያለው ሜታ ለተፈጠረው ስህተት ተጠቃሚዎቹን ይቅርታ ጠይቋል።
ይህ የተጠቃሚዎች ቁጥር ማሽቆልቆል ካጋጠማቸው ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መካከል ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ የሙዚቃ እና የሥነ ጽሁፍ ሙያተኞች ይገኙበታል።
ከእነዚህም መካከል በፌስቡክ ገጹ ላይ ከ2 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች የነበሩት ታዋቂው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ አንዱ ነው። በፌስቡክ ላይ የተከሰተውን ችግር ተከትሎም አሁን የገጹ ተከታዮች ቁጥር ከ10 ሺህ በታች ወርዷል።
በተመሳሳይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች የነበሩት ታዋቂው ፀሐፊ በውቀቱ ስዩም ተከታዮች ቁጥርም በእጅጉ ቀንሶ ከ10 ሺህ በታች ቀንሷል።
እንዲሁም ከግለሰቦች በተጨማሪ በፌስቡክ ገጻቸው ተከታዮች ላይ የቁጥር መቀነስ ከታየባቸው መካከል ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትም ይገኙበታል።