ማንቸስተር ዩናይትድ በአርሰናል በተሸነፈበት ጨዋታ ሆይሉንድ እና ዮሮ ጉዳት ደረሰባቸው

የሰስ እና ዮሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሎስ አንጀለስ በተከናወነ የቅድመ ውድድር የዝግጅት ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ በአርሰናል በተሸነፈበት ጨዋታ አጥቂው ራስመስ ሆይሉንድ እና በ52 ሚሊዮን ፓውንድ ቡድኑን የተቀላቀለው ሌኒ ዮሮ ጉዳት ደርሶባቸው ከሜዳ ወጡ።

ሆይሉንድ 10ኛ ደቂቃ ላይ ከማርከስ ራሽፎርድ የተሻገረለትን ኳስ ከመረብ በማሳረፍ ዩናይትድን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር።

አጥቂው ከ15 ደቂቃ በኋላ ከአሮን ቢሳካ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎል ሲሞክር በደረሰበት የጡንቻ ጉዳት በ25ኛው ደቂቃ ከሜዳ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

የ18 ዓመቱ ዮሮም ለረዥም ደቂቃ ሜዳ ላይ የሕክምና እርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቷል።

ባለፈው ዓመት በርካታ ተጫዋቾችን በጉዳት በማጣት ሲታመስ ለከረመው የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን የሁለቱ ተጫዋቾች መጎዳት አሳሳቢ ሆኗል።

“ስለጉዳታቸው መጠን ለማወቅ 24 ሰዓት መጠበቅ ይኖርብናል” ብለዋል አሰልጣኙ ከጨዋታው በኋላ።

“በተለይም ለኔሊ ተጠንቅቀን ነበር። የሚያሳዝን ነገር ቢሆንም በጎውን እያሰብን የምርመራ ውጤቱን እንጠብቅ” ብለዋል።

የቴን ሃግ ቡድን ጥሩ አጀማመር ቢያሳይም ውጤት ግን አልቀናቸውም።

ጋብሪኤል የሱስ በ25ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን በማገናኘት ቡድኑን አቻ አድርጓል። አጥቂው ጎሉን ሲያስቆጥር ከጨዋታ ውጭ ይመስል ነበር።

ጋብርኤል ማርቲኔሊ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራት ጎል ጨዋታው 2 ለ 1 ተጠናቋል።

ማንቸስተር ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ቪክተር ሊንደሎቨፍ በልምምድ ሜዳ አነስተኛ ጉዳት እንዳጋጠመው ታውቋል።

ትናንት ምሽት ያጋጠሙት ጉዳቶች ለቡድኑ ስጋት ቢሆኑም የሜሰን ማውንት ድንቅ ብቃት ማሳየት ደግሞ ለቡድኑ በበጎ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ያለፈውን ዓመት በብዛት በጉዳት ያሳለፈው ማውንት የቀድሞ ብቃቱን ከማሳየት ባለፈ ወደ ፊት ሲሄድ አደጋ እንደሚፈጥርም የምሽቱ ጨዋታ ያረጋገጠበት ነበር።

ማርቲኔሊ ጎል አስቆጠሯል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአርሰናል በኩል ቡድኑን ይለቃል የተባለው ኤሚል ስሚዝ ሮው በዚህ ጨዋታ አልተሰለፈም። ስሚዝ ሮው ፉልሃምን ሊቀላቀል እንደሚችል የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።

ሪካርዶ ካላፊዮሪ የቡድኑ አዲስ ፈራሚ እንደሚሆን ሲጠበቅ ዴክላን ራይስ እና ቡካዮ ሳካም ከአውሮፓ ዋንጫ መልስ ቡድኑን ይቀላቀላሉ።

የሱስ ድንቅ ምሽት ባሳለፈበት ጨዋታ ማርቲኔዝም ከኮፓ አሜሪካ መልስ ጥሩ ሆኖ አምሽቷል።

“ማርቲኔሊ ከአንድ ልምምድ በኋላ ነው ድንቅ ሆኖ ያመሸው። ይህ የአዕምሮ ጥንካሬ ነው” ብሏል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ።

“ጋብርኤልም ብዙ ተቀይሯል። አሁን ይህንን የሚያስመሰክርበት አጋጣሚ ነው” ሲል አክሏል።

ጨዋታው የተከናውነበት ሜዳ ለዚህ ፍልሚያ በሚል ባደገ ሳር ላይ ሲሆን ለሌላ ዝግጅት ሲባል ከጨዋተው በኋላ ሳሩ ይነሳል ተብሏል።