ቼልሲ ከሲቲ፡ በተጠባቂውን ጨዋታ ፖቸቲኖ የጋርዲዮላን ኃያል ቡድን መቋቋም ይቻላቸዋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቼልሲ በዘንድሮው ውድድር ዓመት ከአንድ እስከ አራት ካሉት ቡድኖች ጋር ተጫውቶ ሽንፈት አላስተናገደም።
እሑድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በሚያደርገው ጨዋታስ ሽንፈት ያስተናግድ ይሆን?
ከሊቨርፑል እና ከአርሰናል ጋር ተጫውቶ አቻ ተለያይቷል። በርካታ ክስተቶችን ባስተናገደው የሰኞው የቶተንሃም ጨዋታ ደግሞ ሦስት ነጠብ አሳክቷል።
የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን “ቼልሲ በዘጠኝ ተጫዋች ከተጫወተው ቶተንሃም ጋር ውጤታማ አልነበረም። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ግን ዕድላቸውን መጠቀም አለባቸው” ብሏል።
ሱተን ይህንን ጨምሮ የ12ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ቅዳሜ

ዎልቭስ ከ ቶተንሃም
ቶተንሃም ከቼልሲ ጋር በነበረው ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾች ወጥተውበትም ፍልስፍናውን ሳይቀይር ተጫውቷል።
ጨዋታው 4 ለ 1 ቢጠናቀቅም አቻ የሚለያዩበት ዕድል ነበር።
ቡድኑ አራት ተጫዋቾችን በጉዳት እና በቅጣት ቢያጣም አጨዋወቱን አይቀይርም።
ዎልቭስ ባለፉት ሳምንታት እየተሻሻለ ይገኛል። ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 1 – 1
አርሰናል ከ በርንሌይ

አርሰናል ቡካዮ ሳካን እና ማርቲን ኦዴጋርድን ጨምሮ የተወሰኑ የተጎዱ ተጫዋቾች አሉት።
ሁለቱ ተጫዋቾች ባይኖሩ እንኳን መድፈኞቹ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በተሸነፉት በርንሌይዎች ፈተና አይገጥማቸውም።
በርንሌይ በሜዳው ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ከሜዳቸው ውጭም የተሻለ ታሪክ የላቸውም።
ኳስ ከኋላ ጀምረው በመመስረት የሚያደርጉትን አጨዋወት ባይቀይሩም ከሳምንት ሳምንት የሚደርስባቸው ሽንፈት በራስ መተማመናቸውን ሸርሽሮታል።
ግምት፡ 3 – 0
ክሪስታል ፓላስ ከ ኤቨርተን
ፓላስ ባለፈው ሳምንት በጥሩ መከላከል እና አጋጣሚዎችን በመጠቀም በርንሌይን አሸንፏል።
በሁለቱ ቡድኖች አጨዋወት ምክንያት ይህ ጨዋታ ተቀራራቢ ፉክክር የሚደረግበት ይሆናል።
ሁለቱም ቡድኖች ኳስ አይዙም፤ ጎሎችንም አያስቆጥሩም።
እንደባለፈው ዓመት ሁሉ ይህ ጨዋታም ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 0 – 0

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ሉተን
ረቡዕ ዕለት ከኮፐንሃገን ጋር በነበረው ጨዋታ ማርከስ ራሽፎርድ በ40ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ እስኪወጣ ድረስ ማንቸስተር ዩናይትድ ጥሩ ተጫውቷል።
ሉተን ደግሞ ምን ያህል ጠንካራ እና አስቸጋሪ ቡድን መሆኑን ባለፈው ሳምንት ከሊቨርፑል ጋር አሳይቷል።
ዩናይትድ ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በፊት የሚያድርጉትን ጨዋታ ማሸነፍ ግዴታ ነው። ቢሸነፉም ግን ኤሪክ ቴን ሃግ ከኃላፊነታቸው አይነሱም።
ዩናይትድ ይህንን ጨዋታ ቢያሸንፍም ጫናው አይቀልለትም።
ግምት፡ 2 – 1
በርንማውዝ ከ ኒውካስል
የተጫዋቾች ጉዳት እየጨመረባቸው ቢሆንም ኒውካስሎች ከማክሰኞው የቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽንፈት በኋላ ሦስት ነጥብ የሚያሳኩበት ጨዋታ ይሆናል።
ኒውካስል ምንም ያህል ጉዳት ቢያስተናግድም ከበርንማውዝ አንጻር ባሉት ተጫዋቾች ማሸነፍ አለበት። የቀድሞው የበርማውዙ አጥቂ ካለም ዊልሰን ጎል ያስቆጥራል ብዬ እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 – 2
እሑድ

አስቶን ቪላ ከ ፉልሃም
ፉልሃም ባለፈው ሳምንት ባለቀ ሰዓት በተቆጠረ ጎል በማንቸስተር ዩናይትድ ቢሸነፍም የአጥቂ መስመራቸው ላይ ጥያቄ አለኝ።
አስቶን ቪላ በኖቲንግሃም ፎረስት መሸነፉ ቢያስገርመኝም በሜዳቸው ግን ጥሩ መሆናቸውን አይተናል።
ዘንድሮ በሜዳቸው ያደረጓቸውን አምስት ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፈዋል።
እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ ከፈለጉ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
ግምት፡ 2 – 0
ብራይተን ከ ሼፊልድ ዩናይትድ
ብራይተን ከአያክስ ጋር በነበረው የአውሮፓ ሊግ ጨዋታ ምክንያት በዚህ ጨዋታ ተጽዕኖ ይኖርባቸዋል።
ሼፊልድ ባለፈው ሳምንት ዎልቭስን አሸንፎ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።
በዚህ ጨዋታ በመከላከል ላይ የተመሠረተ አጨዋወት ይዘው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ግምት፡ 3 – 0
ሊቨርፑል ከ ብሬንትፎርድ

ይህ ለመገመት ከባድ ነው። ብሬንትፎርድ ወደ አቋሙ መመለሱ ጨዋታውን ለመገመት ከባድ ያደርገዋል።
ከአስቸጋሪ አጀማመር በኋላ ብሬንትፎርዶች ከጠንካራ መካለከል ባለፈ በማጥቃቱ ረገድም ጥሩ ናቸው።
በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ሊቨርፑል ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ አለበት። በሜዳቸውም ዘንድሮ ጠንካራ ናቸው።
ግምት፡ 3 – 1
ዌስት ሃም ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ጠንካራ አጀማመር የነበራቸው ዌስት ሃሞች ያለፉትን አራት የሊግ ጨዋታዎች ተሸንፈዋል።
መጥፎ ባይጫወቱም ዴቪድ ሞዬስ አንዳንድ ጎሎችን ያስተናገዱበት መንገድ የሚያስደስታቸው አይመስልም።
ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ሦስት ነጥብ ያሳካሉ። ኖቲንግሃም ከሜዳው ውጭ ጥሩ እየተሻሻለ ቢሆንም ዌስትሃም ያሸንፋል።
ግምት፡ 2 – 1

ቼልሲ ከ ማንቸስተር ሲቲ
ቼልሲው ኒኮላስ ጃክሰን በፕሪሚር ሊጉ አስቀያሚ ሃትሪክ ቢሠራም ሃትሪክ እንደመሆኑ የተጫዋቹን በራስ መተማመን ከፍ ያደርገዋል።
የቼልሲ ድልም በተመሳሳይ የቡድኑን በራስ መተማመን ያሳድገዋል። ብዙዎች ባይገምቱም በምንም መልኩ ይሆን ሦስቱን ነጥብ አሳክተዋል።
ይህ ጨዋታ የሚወሰነው በቼልሲ ሳይሆን በሲቲ አጨዋወት ይሆናል። ሲቲ የተጎዱ ተጫዋቾች ቢኖሩትም ተንካራ ቡድን ስላለው ስጋት አይሆንም።
ማንም ይሰለፍ ሲቲ ሁለት ጎል አስቆጥሮ ያሸንፋል። ጥያቄው ቼል ኳስ እና መረብ ያገናኛል ወይ የሚለው ነው።
ግምት፡ 0 – 2












