ኒው ዮርክ ከተማ በስደተኞች ከፍተኛ ፍልሰት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አወጀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካዋ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ በስደተኞች ከፍተኛ ፍልሰት ምክንያት የተፈጠረውን ቀውስ ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገጉ።
ከሚያዝያ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ከደቡብ የአገሪቷ ድንበር አካባቢ የተነሱ ከ17 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ከተማዋ ገብተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ቴክሳስ፣ አሪዞና እና ፍሎሪዳ ያሉ በሪፐብሊካን ፓርቲ የበላይነት ከሚመሩ ግዛቶች ስደተኞችን ወደ ዲሞክራቶች አካባቢዎች እየላኩ ነው።
ይህም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ድንበር በደረሱበት ወቅት ከዋይት ሐውስ ጋር የነበረው ውዝግብ አካል ነው ተብሏል።
ከመስከረም ወር ጀምሮ በእያንዳንዱ ቀን በአማካይ ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ አውቶብሶች ወደ ኒው ዮርክ እንደሚገቡ ከንቲባ አዳምስ አርብ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ከተማዋ በዘረጋችው የመጠለያ ሥርዓት ውስጥ ከገቡ አምስት ሰዎች ውስጥ አንዳቸው ጥገኝነት ፈላጊ መሆናቸውንም ከንቲባው አክለዋል።
ከንቲባው እንዳሉት አብዛኞቹ ወደ ከተማዋ የገቡት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆቻቸውን የያዙ ቤተሰቦች ሲሆኑ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
ይህ የስደተኞች ፍልሰት በተያዘው በጀት ዓመት ኒው ዮርክን 1 ቢሊዮን ዶላር እያስወጣት ሲሆን፣ ከንቲባዋ የፌደራል እና ሌሎች ግዛቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
“የኒው ዮርክ ነዋሪዎች ተቆጥተዋል፤ እኔም እንደዚያው” ያሉት ከንቲባው፣ “በሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎችን የመደገፍ ሥራ ለመስራት ስምምነት አልነበረም” ብለዋል።
ጨምረውም “ከተማዋ ቅድሚያ ለምትሰጣቸው ጉዳዮች ያላትን ገንዘብ ልታጠናቅቅ ነው። ኒው ዮርክ የምትችለውን ሁሉ እያደረገች ነው፤ ነገር ግን ስደተኞችን ለመርዳት ያለን አቅም እየተሟጠጠ ነው” ብለዋል ከንቲባው።
ከንቲባው የከተማዋ ማኅበራዊ አገልግሎት “ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል በሌሎች እየተበዘበዘ ነው” ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ቴክሳስ፣ አሪዞና እና ፍሎሪዳ ግዛቶች ስደተኞችን በዲሞክራቶች ወደሚመሩ ግዛቶች ይልካሉ።
በድንበር አካባቢ የሚገኙ ግዛቶች ያሉ የሪፐብሊካን ባለሥልጣናት ይህ ስልት የስደተኞች ፍልሰት የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ያለመ ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ እርምጃው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር፣ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ሆኖ በተመዘገበውና በአሜሪካ ደቡባዊ ድንበር በኩል ወደ አገሪቷ የሚገቡ ስደተኞችን ለመቀነስ ሥራ እንዲሰሩ ግፊት ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በዲሞክራቶች የምትተዳደረው ከተማ ኤል ፓሶ፣ ቴክሳስ በከተማዋ ያለውን ጫና ለማቃለል ስደተኞችን ወደ ኒው ዮርክ እና ቺካጎ ለመላክ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠች ነው።
በቴክሳስ ገዢ ከተላኩት በተጨማሪ ኤል ፓሶ ብቻ ወደ 9 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ወደ ሁለቱ ከተሞች አጓጉዛለች።
የኤል ፓሶ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እና ስደተኞቹን ለመርዳት ከመዳረሻ ከተሞች ጋር በመተባበር የተደረገ ነው ብለዋል።
የኒው ዮርክ ከንቲባ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመደገፍ እና ማንኛውንም የምላሽ ጥረቶችን ለማፋጠን ከተማዋ ያላትን እንድትሰጥ የሚያስችለውን የማስፈፀሚያ ትዕዛዝ አውጥተዋል።
የቴክሳስ ገዢ ግሬግ አቦት ቃል አቀባይ በበኩላቸው አርብ ዕለት የኒው ዮርክ ከንቲባ ያወጡትን አዋጅ ውድቅ አድርገውታል።
“እውነተኛው አስቸኳይ ጊዜ ያለው ትናንሽ የቴክሳስ ከተሞች የሚገኙበት ደቡባዊ የአገሪቱ ድንበሮች በየቀኑ በመቶዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች ሲጨናነቁ እና የባይደን አስተዳዳር እዚያ ሲጥላቸው ነበር” ብለዋል ቃል አቀባይዋ ሬኔ ኢዜ።
ቃል አቀባይዋ ኢዜ አክለውም እስከ ጥቅምት ድረስ ቴክሳስ ወደ ግዛቷ የገቡ 3 ሺህ 100 የሚጠጉ ስደተኞችን ከ60 በላይ በሚሆኑ አውቶብሶች በማሳፈር ወደ ኒው ዮርክ ልካለች ብለዋል።












