ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ በአንድ ትምህርት ቤት በቀድሞ ተማሪ በተከፈተ ተኩስ ስድስት ሰዎች ተገደሉ
በአሜሪካዋ ቴኔሲ ግዛት፣ ናሽቪል ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ በቀድሞ ተማሪ በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሕጻናት እና ሦስት ሠራተኞች ተገደሉ።
በኮቬናንት ትምህርት ቤት የተገደሉት ሦስቱ ሕጻናት ዕድሜያቸው ዘጠኝ እና ከዘጠኝ ዓመት በታች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ፖሊስ የሟቾቹን ማንነት ለይቶ ይፋ አድርጓል።
ባለቤትነቱ የግል የሆነው የክርስቲያን ትምህርት ቤት ወደ 200 የሚጠጉ ተማሪዎች ያሉት ሲሆን ዕድሜያቸው ከሦስት እስከ 12 የሚደርስ ሕጻናትን ያስተምራል።
በጥቃቱ ከተገደሉት ሠራተኞች መካከል አንዷ የሆነችው የ61 ዓመቷ መምህርት ሲይሺያ ፒክ፣ ግድያው ሲፈፀምባት በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሥራ ላይ ነበረች።
ሌላኛው የ61 ዓመቱ ማይክ ሂል ደግሞ የጽዳት ሠራተኛ ሲሆን የ60 ዓመቷ ካትሪን ኮንስ ደግሞ የትምህርት ቤቱ ኃላፊ እንደነበረች በትምህርት ቤቱ ድረ ገጽ ላይ ተገልጿል።
ፖሊስ የአስቸኳይ እርዳታ ጥሪውን ሰኞ ዕለት ከቀኑ 9፡13 እንደተቀበለ ገልጿል።
ግድያውን በመፈፀም የተጠረጠረችው በተፈጥሮ ያገኘሁኝ ጾታ አይወክለኝም በሚል ትራንስ ጀንደር ሴት ነኝ ያለችው የ28 ዓመቷ ኦድርይ ሃሌ መሆኗን ፖሊስ ገልጿል።
በከፊል አውቶማቲክ የሆነ የጦር መሣሪያን ጨምሮ ሦስት ሽጉጦችን ታጥቃ ጥቃቱን ስትፈፅም የነበረችው ሃሌ፣ በኋላ ላይ በፖሊስ በተተኮሰባት ጥይት ተገድላለች።
ተጠርጣሪዋ ወደ ትምህርት ቤቱ አሽከርክራ በመጓዝ ተዘግተው ከነበሩት የትምህርት ቤቱ በሮች በአንደኛው ላይ በመተኮስ ወደ ግቢው ዘልቃ ሊትገባ ችላለች።
የናሽቪሊ ፖሊስ ባወጣው ቪዲዮ፣ ሃሌ ወደ ውስጥ ለመግባት በዋናው በር ያለውን መስታወት በያዘችው መሳሪያ ሰብራ በመግባት ጭር ባሉት የትምህርት ቤቱ መተላለፊያዎች[ ኮሪደሮች] ዓይኗን ስታማትር እና አንድ ቦታ ላይ ‘የሕጻናት ሚኒስቴር’ በሚል የተጻፈበትን ክፍል በኩል ስታልፍ ያሳያል።
ከደኅንነት ካሜራዎች ከተወሰደው ምሥል ላይም ሃሌ የጥይት መከላከያ የመሰለ ሰደርያ[ ቬስት] ለብሳ በአንድ እጇ የጦር መሣሪያ ይዛ፣ በግራ ወገቧ አካባቢ ተመሳሳይ መሣሪያ ሻጥ አድርጋ ትታያለች።
ሃሌ ወደ ሁለተኛው ፎቅ ከማምራቷ በፊትም በትምህርት ቤቱ የምድር ወለል ላይ ተኩሳለች።
የፖሊስ መኪና እንደደረሰም ሃሌ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ሆና በፖሊሶቹ ላይ ተኩስ ከፍታ እንደነበር ፖሊስ ተናግሯል።
በዚህም አንድ የፖሊስ መኮንን በስብርባሪ መስተዋት ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን ፖሊስ በፍጥነት ወደ ሕንጻው በመግባት ተጠርጣሪዋን ተኩሶ ገድሏታል።
በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ በቆመ መኪና ላይ በተደረገ ፍተሻ ሃሌ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ እንደነበረች እንዲያምኑ እንዳደረጋቸው መርማሪዎች ገልጸዋል።
የናሽቪሊ ፖሊስ አዛዥ ጆን ድራኬ እንዳሉት በስፍራው ያሉ መርማሪዎች ተጠርጣሪዋ ይህንን ጥቃት እንዴት ልትፈጽም እንደምትችል የሚያመላክት መመሪያ እና የትምህርት ቤቱን መግቢያ እና መውጫ በሮችን ጨምሮ የሚያሳይ ካርታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የአንድ ተማሪ እናት በጥቃቱ ልጇ ተረብሾ እንደነበር ገልጻለች።
“ አሁን ላይ ገዳይዋ መገደሏን ሲያውቅ ደኅና እየሆነ ነው” ስትል እናት ሻውንድል ብሩክስ ለቢቢሲ ተናግራለች። “ ይህ ልናወራው የሚገባ ጉዳይ መሆን አልነበረበትም። ልጆቻችንን እያሳጣን ነው” ስትልም አክላለች።
የናሽቪሊ ከንቲባ ጆን ኩፐር በሰጡት መግለጫ ከተማዋ “ ትምህርት ቤቷ አስደንጋጭ ጥቃት አስተናግዳለች” ሲሉ ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም ጥቃቱን ‘የቤተሰብ አስከፊ ቅዠት’ ሲሉ ጠርተውታል።
“ የጦር መሣሪያ ጥቃትን ለማስቆም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል” ያሉት ፕሬዚደንቱ፣ ኮንግረሱ የጦር መሣሪያ ሕጉን እንዲያጸድቅ በድጋሜ ጥሪ አቅርበዋል። “ ማኅበረሰባችንን እየከፋፈለ እና የሕዝባችንን ሕይወት እየነጠቀ ነው” ብለዋል ፕሬዚደንቱ።
የአሁኑ ጥቃት በአሜሪካ ለ129ኛ ጊዜ የተፈፀመ መሆኑን የጦር መሣሪያ የጅምላ ጥቃት መረጃዎችን የሚከታተለውና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ገን ቫዮለንስ አርካይቭ አስታውቋል።
በኢዱኬሽን ዊክ እንደተጠናቀረው መረጃ ከሆነ ደግሞ በዚህ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ እስከ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ በአሜሪካ ሞትና እና ጉዳት ያስከተሉ በትምህርት ቤቶች የተፈፀሙ 12 ጥቃቶች አጋጥመዋል።