የቺካጎ ከንቲባ ትራምፕ በከተማዋ ሊወስዱ ያሰቡትን እርምጃ ለመከላከል የሚያስችል ትዕዛዝ ፈረሙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቺካጎ ከተማ ከንቲባ፤ የትራምፕ አስተዳደር በከተማው በሚገኙ ስደተኞችን ላይ እንደሚወስድ የዛተውን እርምጃ እንዴት መካላከል እንደሚቻል በሚዘረዝረው 'ፕሮቴክቲንግ ቺካጎ ኢኒሺየቲቭ' የተባለ ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸው አኖሩ።

ዲሞክራቱ የቺካጎ ከንቲባ ብራንደን ጆንሰን፤ "ከተማችን ላይ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ እና ሕገ ወጥ ወታደራዊ ወረራ አያስፈልግም፣አንፈልግምም" በማለት ተናግረዋል።

ከንቲባው የፈረሙት ትዕዛዝ፤ የከተማው ተቋማት ሊካሄዱ ለሚችሉ የኢሚግሬሽን ማስከበር እርምጃዎች እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው መመሪያ ይሰጣል።

ትራምፕ ከሳምንታት በፊት 2,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ያሰማሩ ሲሆን ይህንን አካሄድ "ሁከት" ሲሉ በጠሩት ቺካጎ ከተማም እንደሚደግሙ ዝተዋል። በተጨማሪም አስተዳደሩ በከተማው የሚሰማሩ የፌዴራል የኢሚግሬሽን አካላት ቁጥርን ለመጨመር እያቀደ መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ፤ የከንቲባ ጆንሰንን ትዕዛዝ "የልታይ ባይነት እርምጃ" ሲሉ ገልጸውታል።

አሁን የተፈረመው ትዕዛዝ፤ ዋይት ሐውስ እንዲሁም የኢሊኖይ ግዛት እና በአካባቢው ባለሥልጣናት አመጽ የተቀላቀለባቸው ወንጀሎችን ለመቆጣጠር በያዙት አቋም ምክንያት እየተካረረ የመጣው ውጥረት አዲስ ምዕራፍ ነው።

ትዕዛዙ፤ትራምፕ እና የፌዴራል አካላት "የአሜሪካን የጦር ኃይሎች በከተማው ውስጥ ለማሰማራት ከሚያደርጉት ሙከራ ሁሉ እንዲቆጠቡ" ይጠይቃል።

ከተማው ያሉትን ፖሊሲዎች በድጋሚ የሚያጸናው ይህ ትዕዛዝ፤ የሕግ አስከባሪ መኮንኖች በሰውነት ላይ የሚገጠሙ ካሜራዎችን እና ስለ ማንነታቸው የሚገልጽ መለያ መረጃዎችን እንዲያደርጉ ያስገድዳል። የጸጥታ አካላት ጭምብል እንዳይለብሱም ያግዳል።

"አይስ" እየተባለ የሚጠራው የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ ሕግ አስከባሪ ተቋም መኮንኖች በሌሎች ከተማዎች ማንነታቸውን በመደበቅ በሚወስዷቸው እርምጃዎች ምክንያት ከፍተኛ ትችት ደርሶባቸዋል።

ከንቲባ ጆንሰን እንደሚናገሩት፤ ነዋሪዎች የኢሚግሬሽን አካላት በሚያጋጥሟቸው ጊዜ ምን ዓይነት መብቶች እንደሚኖራቸው በከተማው ባለስልጣናት ገለጻ ይደረግላቸዋል።የአካባቢው የጸጥታ አካላት የፌደራል መኮንኖች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ላይ እንደማይሳተፉም ገልጸዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት እንደሚገልጹት ከከተማው አምስት ነዋሪዎች አንዱ ስደተኛ ነው። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከላቲን አሜሪካ አገራት የመጡ መሆናቸውንም ይናገራሉ።በቺካጎ ከሚኖሩት እነዚህ ስደተኞች መካከል ምን ያህሉ ሰነድ አልባ እንደሆኑ ግልጽ አይደለም።

የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ትራምፕ፤ሦስተኛው የአሜሪካ ትልቅ ከተማ "የግድያ ሜዳ" እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ በከተማው የሚፈጸመው ወንጀል መጠን የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ የሚያስወድ ነው በማለት ይከራከራሉ።

ኢሊኖይ ገዥ ጄ ቢ ፕሪስከር፤ ትራምፕ የአገሪቱን ብሔራዊ ዘብ በቺካጎ እንደሚያሰማሩ መግለጻቸውን በመቃወም ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ነው ሲሉ ተችተዋል።

ዴሞክራቱ ፕሪስከር፤ "ዶናልድ ትራምፕ ቀውስ ለመፍጠር መሞከር፣ ዩኒፎርም ለብሰው የሚያገለግሉ አሜሪካውያንን የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ እና ሠራተኛ በሆኑ ቤተሰቦች ላይ ያስከተሉትን ስቃይ ለማዘናጋት ሥልጣናቸውን አላግባብ መጠቀም ቀጥለዋል" በማለት ወቅሰዋል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አቢጌል ጃክሰን፤ የቺካጎ ባለስልጣናት ወንጀልን መከላከልን የውግንና ጉዳይ እያደረጉት ነው ብለዋል።

"እነዚህ ዴሞክራቶች ፕሬዝዳንቱን ለመተቸት በሚል ከሚወስዷቸው የሕዝበኝነት እርምጃዎች ይልቅ በገዛ ከተሞቻቸውን የሚፈጸመውን ወንጀልን በማስተካከል ላይ ቢያተኩሩ ኖሮ የማህበረሰባቸው ደህንነታቸው እጅጉን የተጠበቀ ይሆናል" በማለት ባለስልጣናቱን ተችተዋል።