ኡጋንዳ ከ50 ዓመት በፊት በኢንቴቤ ለተገደው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድም ሐውልት አቆመች

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቅ ወንድም ዮናታን ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, GPO via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቅ ወንድም ዮናታን ኔታንያሁ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኡጋንዳ ከ50 ዓመት በፊት በኢንቴቤ የታገቱ ሰዎችን ለማዳን በተካሄደ ዘመቻ ላይ ለተገደለው ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድም ዮናታን ኔታንያሁ ሐውልት አቆመች።

የኡጋንዳ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሙሁዚ ካይነሩጋባ ሐውልቱ ጀግንነቱን እና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አገልግሎትን የሚዘክር መሆኑን ተናግረዋል።

ከ50 ዓመት በፊት ሁለት ፍልስጤማውያን እና ሁለት ጀርመናውያን ከቴል አቪቭ የተነሳውን ኤር ፍራንስ ጠልፈው ወደ ኡጋንዳ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያመራ ካደረጉ በኋላ በተካሄደውና ከ100 በላይ ታጋቾችን ነጻ ባወጣው ዘመቻ የተገደለው ብቸኛው የእስራኤል ወታደር ኔታንያሁ ነበር።

ካይኔሩጋባ ይህንን ወታደራዊ ዘመቻ "በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ ጉልህ ከሆኑት ክስተቶች አንዱ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ በሁለቱ አገራት መካከል አሁን ያለውን የጠበቀ ግንኙነትም "አስደናቂ ጉዞ" ሲሉ አወድሰውታል።

ሐውልቱ የቆመው እገታው በተፈጸመበት አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ከመንገደኞች ማስተናገጃ ፊት ለፊት ሲሆን፣ ዮናታን ኔታንየሁ በእጁ መሣሪያ ይዞ ወደፊት ሲራመድ ያሳያል።

በዚህ ታጋጆችን ለማስለቀቅ በተካሄደ ዘመቻ ወቅት ሦስት ታጋቾች ዣን ዣክ ሚሙኒ፣ ፓስኮ ኮሄን እና አይዳ ቦሮቾቪች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ዶራ ብሎክ ደግሞ በኋላ ላይ በዋና ከተማዋ ካምፓላ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላት ሳለ ተገድላለች።

"የእነዚህ ሰማዕታት ተግባር መጪው ትውልድ ሰላም፣ ፍትህ እና ሰብአዊ ክብርን እንዲያስቀድም አርዓያ ሆኖ ይቀጥል" ሲሉ የጦር አዛዡ ተናግረዋል።

ጠላፊዎቹ እና በኡጋንዳ የተቀላቀሏቸው ሦስት ተባባሪዎቻቸው እንዲሁም 45 የኡጋንዳ ወታደሮች ታጋቾቹን ለማስለቀቅ በተደረገ ዘመቻ ወቅት ተገድለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ካይንሩጋባ የወታደሮቹን ሞት በመጥቀስ "ትክክለኛ ነው ብለው ላመኑበት ነገር በጀግንነት ተዋግተዋል። እርግጥ ነው፣ ዛሬ፣ የኢዲ አሚን መንግሥት የኡጋንዳ ሕዝብን የማይወክል ጨካኝ አምባገነን መንግሥት መሆኑን እናውቃለን" ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 27/1976 ከቴል አቪቭ ተነስቶ ወደ ፓሪስ ይበር የነበረው አውሮፕላን አቴንስ በቆመበት ወቅት ነው የፍልስጤም ነፃ አውጪ ግንባር አባል የሆኑት ጠላፊዎች የተሳፈሩት።

ከዚያም አውሮፕላኑን ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ሊቢያ እንዲበር እና ነዳጅ እንዲሞላ ካደረጉ በኋላ ኡጋንዳ እንዲበር አድርገዋል።

ከዚያም ኤርባስ ኤ300 ወደ ኡጋንዳ ሄዶ ኢንቴቢ ሲያርፍ በወቅቱ የአገሪቱ መሪ የነበሩት ኢዲ አሚን በደስታ ተቀብለዋቸዋል።

አውሮፕላን ያገቱት ግለሰቦች 5 ሚሊዮን ዶላር እና በእስራኤል፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በስዊዘርላንድ እና በኬንያ የታሰሩ 53 ታጣቂዎችን እንዲፈቱ ጠይቀዋል። አንዳንዶቹ ታጋቾች እአአ ሰኔ 30 እና ሐምሌ 1 ሲለቀቁ እስራኤላውያን እና አይሁዶች ግን እንዲቆዩ ተደርገዋል።

እአአ ሐምሌ 3 ከእስራኤል ተነስተው በኬንያ በኩል የበረሩ ከፍተኛ ኮማንዶዎች ኢንቴቤ ካረፉ በኋላ ከ90 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ታጋቾቹን ማስለቀቅ ችለዋል።

የሕይወት ማዳን ዘመቻው በእስራኤል እንደ ትልቅ ድል ሲቆጠር ለኢዲ አሚን ግን በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት ከፍተኛ ውርደት ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአስር ዓመት በፊት ወደ ኢንቴቤ በመጓዝ ስፍራውን ሲጎበኙ "ሽብርተኞችን ለማሸነፍ ሁለት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ከወንድሜ ተምሬያለሁ፤ እነሱም ግልጽነት እና ድፍረት ናቸው" ብለዋል።

ኬይኔሩባ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የሆነውን ነገር "በታሪካችን ውስጥ ጠባሰ የጣለ ምዕራፍ" ሲሉ ጠርተውታ።

ነገር ግን የኡጋንዳ እና የእስራኤል ግንኙነት "በጋራ መተማመን፣ መከባበር እና ትብብር የሚገለጽ አጋርነት" ሆኗል ብለዋል።