ሁለት የአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተሮች ተከስክሰው ሰዎች መሞታቸው ተሰማ

ብላክሃውክ የተሰኘው ሄሊኮፕተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአሜሪካዋ ኬንታኪ ግዛት ሁለት የጦር ሄሊኮፕተሮች ተከስክሰው ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።

የግዛቲቷ አስተዳዳሪ አንዲ በሽያር “የሄሊኮፕር አደጋ መድረሱ እና ሞትም እንደሚጠብቁ መግለጹ ከባድ ዜና ነው” ብለዋል።

ክስተቱ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሃያ አምስት ጉዳይ ለአራት እንዳጋጠመና እስከ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውንም የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የአከባቢው ጦር ሄሊኮፕተሮቻቸው በአደጋው መከስከሳቸውን አረጋግጠዋል።

የጦር ሄሊኮፕተሮቹ የተከሰከሱት ትልቅ ከሚባለው ፎርት ካምቤል የጦር ሰፈር አቅራቢያ በሚገኘው ትሪግ ካውንቲ መሆኑም ተገልጿል።

ኤችኤች 60 ብላክሃውክ የተሰኙ ሁለት ሄሊኮፕተሮች “በተለመደ የስልጠና ተልዕኮ በነበሩበት ወቅት” መከስከሳቸውን የፎርት ካምቤል ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል።

“የጦር ሄሊኮፕተሩ አብራሪዎችም ሆነ ሰራተኞች ሁኔታ ለጊዜው አይታወቅም” ብለዋል።

“በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት አባላቱን እና ቤተሰቦቻቸውን በመንከባከብ ላይ አተኩረናል” ሲሉም አክለዋል።

የጦር ሄሊኮፕተሮቹ የመክስከሳቸው ክስተት በምርመራ ላይ መሆኑን እና ተጨማሪ መረጃ ሲገኝም ይፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የፎርግ ካምቤል የጦር ሰፈር ከትሪግ ካውንቲ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

እነዚህ የጦር ሄሊኮፕተሮች የ101ኛው የአየር ወለድ ክፍል አካል መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም በአሜሪካ ጦር ውስጥ ብቸኛው የአየር ጥቃት ክፍልና በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ ግጭት ዞኖች የሚላኩ ናቸው።